ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት ደቡብ ወሎን ሰብሮ በማለፍ አገር የማፍረስ ሕልሙ አልተሳካለትም

 አዲስ አበባ (ኢዜአ)  መስከረም 10/2014 አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ደቡብ ወሎን ሰብሮ በማለፍ አገር የማፍረስ ሕልሙ እንዳልተሳካለት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሀመድ ተናገሩ።

የሽብር ቡድኑ በእብሪት ተነሳስቶ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ወሎን የትርምስ ቀጠና ማድረጉን ገልጸዋል።

ይሁንና በአገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ጠንካራ መልሶ ማጥቃት እየተመታ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በወረባቦ፣ በተሁለደሬና አምባሰል ወረዳዎች አቅጣጫ ጠላትን በመምታት አመራሩ ሳይቀር በጦር ግንባር አመርቂ ድል እያስመዘገበ ነው ብለዋል።

አሸባሪው የህወሓት ወራሪ ኃይል ደቡብ ወሎን ሰብሮ በማለፍ አገር የማፍረስ ሕልሙ በማይሳካበት ሁኔታ ከፍተኛ ምት እያረፈበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ ሰይድ የአካባቢው ሚሊሻ፣ ሕዝቡና ወጣቱ የስንቅና ትጥቅ ድጋፍ በማድረግ እያደረገ ያለው ቅንጅታዊ ተጋድሎ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ወራሪውን ሃይል ለአማራ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ስጋት በማይሆንበት መንገድ መቅበር የሚያስችል አቅም መፈጠሩንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው ጦርነቱን በድል ለማጠናቀቅ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ላለው የደጀንነት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም