ቀጥታ፡

የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቋቋም የኢትዮጵያን እውነታ ማሳየት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

መስከረም 09/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን በአገሪቷ ላይ እየተደረጉ ያሉ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመመከት ትክክለኛውን ነባራዊ ሁኔታ ማሳየታቸውን እንዲያጠናክሩ ምሁራን መከሩ።

የስትራቴጂክ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት "የውጭ ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ" በሚል ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር መክሯል።

የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት ምንነት፣ መገለጫ ባህሪያትና የውጭ ጣልቃ ገብነት በተለያዩ አገራት እንዲሁም በኢትዮጵያ በሚሉ ርዕሶች ፅሁፍ አቅርበዋል።

ዕጩ ዶክተር ጋሻው አይፈራም የውጭ ጣልቃ ገብነት ምንነትና መገለጫ ባህሪያትን በዳሰሰ ፅሁፋቸው አገራት ለምንና እንዴት ጣልቃ እንደሚገቡ ከኢትዮጵያ ጋር አያይዘው ተንትነዋል።

የኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሠላም መመለስ፣ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ትብብር በአሜሪካና ኬንያ እንደ ብሔራዊ ስጋት መታየትን ለጣልቃ ገብነት አንድ ምክንያት መሆኑን አመላክተዋል።

አብዛኛው ጫና ከሕዳሴ ግድብና ከአሸባሪው የህወሓት ጦርነት ጋር ቢያያዝም ከጂኦ ፖለቲካ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር እርስ በእርሱ የተሳሰረ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዶክተር ዳርእስከዳር ታዬ በበኩላቸው ጣልቃ ገብነት በአገራት ላይ ያስከተለውን ጉዳት የአፍጋኒስታንና የመንን ሁኔታ አንስተው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ሁኔታም ከለውጡ ወዲህ እየተደረጉ ያሉ የዲፕሎማሲ፣ የሚዲያና ሌሎች ጫናዎች ላይ ትኩረት በማድረግም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ እያከናወነች ያለችው የልማት ስራ የፈጠረው ስጋት፣ ቀጣናውን ለመቆጣጠር ያለ ፉክክር፣ የአሜሪካ አዲሱ አስተዳደር ዓለምን ለመምራት ይዞ የመጣው እሳቤ እንደፈለገው አለመሄድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠር ፍላጎት ምንጭ ካሏቸው መካከል ዘርዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ የነበሩ የመንግስታት ድጋፎችና የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ከተደረገ በኋላ ጫናዎች መበርታታቸውን አውስተዋል።

ከመንግስታት በተጨማሪም  ስለ ኢትዮጵያ በጎ ነገር ያሰራጩ የነበሩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ዘመቻ መክፈታቸውን ነው ያመለከቱት።

አብዛኞቹ የሚያሰራጩት መረጃ የኢትዮጵያን ስም የሚያጠፋ፣ የፖሊሲ አውጪዎች አስቀድመው ለጫና እንዲዘጋጁ በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ በር የሚከፍቱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ዶክተር ወርቁ ያዕቆብም መንግስት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ዳያስፖራውና ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና ለመቋቋም ሊሰሩ ይገባል ያሉትን ተግባር ጠቁመዋል።

"ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ዘመቻ ለመመከት የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ መሆን አለባቸው" ነው ያሉት። 

በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ተግባቦት ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችን አጠቃቀም በማጎልበት የመረጃ ክፍተትን ለመሙላት በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ምዕራባዊያን "ጣልቃ ለመግባት ምክንያታቸው የተቀደሰ በማስመሰል በመጀመሪያ በሚዲያ ነው የሚሰሩት" ብለዋል።

ይህም ጥፋተኛ ያልሆነን አገር ጥፋተኛ በማስመሰል የሚወስዱት እርምጃ ትክክለኛ እንደሆነ የሚያደርጉት አጀንዳ የማስያዝ ተግባር መሆኑን አክለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ በመሆን መስራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።

የኢትዮጵያ እውነት ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉ መረጃዎችን በማሰራጨት የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን የተለያዩ የመረጃ አውታሮችን በመጠቀም ማክሸፍ እንደሚገባም እንዲሁ።

በውይይቱ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ከውጭና ከውስጥ ከገጠማት ፈተና እንድትወጣ መረጃ የማድረስ ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም