ቀጥታ፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል---የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ  መስከረም 9/2014 (ኢዜአ)  ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የልማትና የብልጽግና ጉዞ በማፋጠን ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጫና ስለሚያቃልል ለግንባታው መጠናቀቅ የምናደርገውን ድጋፍ እናጠናክራለን ይላሉ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች።

የ8ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ታዳጊ ራኬብ ጌታቸው የግድቡ መጠናቀቅ ከሚያጓጓቸው ሰዎች መካከል አንዷ ናት።

‹‹ግድቡኮ እኩያዬ ነው፤ የኔና ዘመን ምልክት ነው፣ ማንነት ነው፣ ተስፋችንም ነው ›› ትላለች ተማሪች ራኬብ። ሰራተኛ ባለመሆኗ ለግድቡ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ ለማበርከት ገቢ ባይኖራትም ወላጆቿ ለሷ ያሉትን እስም ለግድቡ ማድረግን መርጣለች።

‹‹እኔ ገንዘብ የለኝም፤ ነገር ግን ቤተሰቦቼ ለአዲስ ዓመት ልብስ እንድገዛበት በመደቡልኝ 2ሺህ ብር ቦንድ ገዝቼበታለሁ›› ብላለች፡፡

“ይህ በቂ አይደለም፤ ስለግድቡ ያነበብኩትን፣ የሰማሁትን፣ ለኢትዮጵያችን የዕድገት ምንጭ መሆን ለትምህርት ቤቶች ክበባት በማሳወቅ ተማሪዎች ቦንድ እንዲገዙ እቀሰቅሳለሁ” ትላለች፡፡

ይህ ግድብ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር ኢትዮጵያን የተሻለችና የበለጸገች አገር እንድትሆን መንገዶች ሁሉ ክፍት ይሆናሉ የምትለው ተማሪ ራኬብ ጠላቶችን በጋራ መከላከል ብቻ ሣይሆን ለግድቡ መጠናቀቅ ሁሉም መደገፍ እንዳለበት ገልፃለች።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ድሬዳዋ ገብቶ በየቀበሌው መዘዋወር ከጀመረ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በከተማይቱ የተለያዩ ቀበሌዎች የዋንጫውን መግባት ተከትሎ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ራኬብም በዚህ ዙሪያ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የቀበሌ 03 መስተዳድር እሷን ጨምሮ ለግድቡ ግንባታ ቦንድ ለገዙት ባለሃብቶችና ማህበራት የዕውቅናና የምስክር ወረቀት ሰጥቷል።

ዕውቅና የተቸራቸው ባለሃብቶችና ማህበራት ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ልክ እንደ ተማሪ ራኬብ ሁሉ ግድቡ ተጠናቆ ለአገር ብርሃን እስኪረጭ ድረስ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ዕውቅና የተቸራቸው ባለሃብቶች መካከል አስመጪና ላኪ የሆኑትና የ50 ሺህ ብር ቦንድ የገዙት አብዱልዋሲ አህመድ እንደተናገሩት፤ መጪው የኢትዮጵያ ዕድገት ዕውን መሆን የሚረጋገጠው በህዳሴው ግድብ ነው፡፡

አገሪቷ ያላት ትልቅ ተስፋ ነው፤ የአሁንም የወደፊቱ ትውልድ የማንነትና የዕድገት ምልክት ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

‹‹ግድቡ ዕውን ሲሆን መሠረተ-ልማቶች ይስፋፋሉ፤ አገራችን በኤሌክትሪክ ራሷን በመቻል በመስኖ ልማትና በኢንዱስትሪ መስክ የተሻለችና የበለፀገች አገር መሆኗ አይቀርም፤ ይህን የሚጠላ የለምና አሁንም ድጋፋችንን ማጠናከር አለብን››ብለዋል፡፡

ተመሣሣይ ሃሳብን የሚጋሩትና 4 መቶ አባላት ያሉት የአስቤዛ ሸማቾች ማህበር ተወካይ አቶ ደረጀ ወርቁ በራሳችን ሃብትና ዕውቀት ግድቡን እንደጀመርነው ሁሉ እስከመጨረሻው ድረስ ተቀናጅተን ድጋፋችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

ግድቡ ዕውን እንዲሆን ከውጭና ከውስጥ የተነሱብንን ጠላቶች ለመደምሰስ የማህበሩ አባላት ግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

‹‹አሁን የ30 ሺህ ብር ቦንድ ገዝተናል፤ ድጋፋችን እስከመጨረሻው ይቀጥላልም ›› ብለዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ምልክት የሆነው ዋንጫ በከተማው ከ03 ቀበሌ ወደ 04 ቀበሌ ርክክብ በተካያሄደበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት ለግድቡ ዳር መድረስ ቦንድ ለገዙትና የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉት ምስጋና ያቀረቡት አቶ ከድር ጁሃር ናቸው፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊና የድሬዳዋ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሣትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ከድር ጁሃር የኢትዮጵያ ከፍታ የሚረጋገጥበትና በኢትዮጵያዊያን አንጡራ ሃብት፣ ዕውቀትና ገንዘብ እየተገባደደ የሚገኘውን ግድብ በተቀናጀ ርብርብ ዕውን ይሆናል ብለዋል፡፡

ይሄንን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ በውጭና በአገር ውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማቀጨጭ የሚደረገው ጥረት ፍጹም አይሳካም ይላሉ አቶ ከድር።

በተፈጥሮ ሃብታችን የመልማት መብታችንን ለማፈን የሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት አሁንም በተባበረ ህዝባዊ አንድነት መና ለማስቀረት መረባረብ እንደሚገባም ነው አቶ ከድር ያሳሰቡት ሃላፊው “ግድቡ የኢትዮጵያን የብልጽግና ማብሰሪያ ምልክት ነው›› ብለዋል፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ምልክት የሆነው የህዳሴ ዋንጫ ድሬዳዋ ከገባ ጀምሮ ህዝቡ ለግድቡ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በውስጥም በውጭም ያሉ አንዳንድ አካላት ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ቀርቦ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በሶስቱ ሃገራት ድርድር እንዲፈታ መወሰኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም