የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው
አዲስ አበባ መስከረም 9/2014 (ኢዜአ) "የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የያዘው አቋም ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና ሁላችንም የምንቃወመው ነው" ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጋሞ ተወላጆች ተናገሩ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያነጣጠረ" በሚል አዲስ የማዕቀብ ትዕዛዝ መፈረማቸው እየተነገረ ይገኛል።
የፕሬዚዳንቱ ተግባር የአገርን ህልውና እየተፈታተነ ታሪክና ቅርስን እንዲሁም ሃይማኖታዊ ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም፣ ንፁሃንንም በመጨፍጨፍ ላይ የሚገኘውን አሸባሪ የህወሃት ቡድን አድሜ ለማራዘም ያለመ ነው።
የአሸባሪው ተጨባጭ እንቅስቃሴ ይህ መሆኑ እየታወቀ የአሜሪካው ፕሬዚዳነት የማእቀብ የመጣል ፊርማ ማኖራቸው ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሁሉ እየተቃወሙት ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጉዳዩን አስመልክቶ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ አሜሪካ በኢትዮጵያን ላይ እያራመደችው ያለው ፖሊሲ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የጋሞ ተወላጆች፤ "ኢትዮጵያዊያን በአገራችን ክብር እና ህልውና የማንደራደር ህዝቦች መሆናችንን ሁሉም የሚያወቅው እውነታ ነው" ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ለሚሞክር የትኛውም ወገን እጅ የማይሰጡ፣ ኩሩ እና ጀግኖች የተወለዱባት አገር መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ከተለያዩ አቅጣጫዎች ኢትዮጰያን ለማፍረስና ለመበታተን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአሜሪካ መነግስት አቋም ፍጹም ተቀባይነት የሌለውና ሁሉም የሚቃወመው መሆኑን የተና\ገሩት አቶ ጫቶ ጫላ ናቸው።
አሜሪካ በኢትዮጵያ የወስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነቷን በመወጠል ማዕቀፎችን በመጣልና ከአሸባሪው ህወሃት ጋር ድርድር አንዲደረግ ግፊት የምታደርግበት አግባብ ትክክል አለመሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ሃይዲያ ካንሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንድትበታተን፣ እንድትፈርስ እና ጠንካራና ልማታዊ አገር እንዳትሆን የሚሹና አካላትን በተባበረ ክንድ መመከት ያስፈልጋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ አህመድ በዚህ ዙሪያ በግልፅ ደብዳቤታቸው ለጆ ባይደን ያስተላለፉት መልዕክት ተገቢ እና ወቅታዊውን የአገሪቱን ሁኔታ ያገናዘበ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
"የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት በአገሪቱ ላይ እየሄደ ያለው አካሄድ አገሪቱን ከአንድነቷ ይልቅ እንድትበታተን፣ እንድትፈርስ ጠንካራና ጤናማ አገር ሆና እንዳትቀጥል የማድረግ አካሄድ መሆኑን እየተሄደ ያለውን ጉዳይ መንግስት የነቃ ይመስለኛል'' ያሉት ደግሞ አቶ ሃብታሙ ቃሎ ናቸው፡፡
አክለውም አሁን ባለው አካሄድ ከህወሀት ጋር የአገሪቱ መንግስት ወደ ድርድር አንዲመጣ የምታደርገው ግፊት የኢትዮጵያ መንግስት ጠንካራ መሰረትን ጤናማ ስራዎችን እየሰራ ባለበት ወቅት አፍሪካን የመቆጣጠሯን ራዕይ የሚያጨልም አካሄድ ስለመሰላት መንግስት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እምነታቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን በማጠናከርና በጋራ መቆም የውጭና የውስጥ አፍራሽ ሃይሎችን እንዲመክቱም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።