የእሬቻ በዓልን በድምቀት ለማክበር በምዕራብ አርሲ ዞን ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የእሬቻ በዓልን በድምቀት ለማክበር በምዕራብ አርሲ ዞን ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 9/2014(ኢዜአ) ሻሸመኔ መስከረም 09/2014 (ኢዜአ) የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ የሆነውን የእሬቻ በዓልን በደማቅ ስነ-ስርዓት ለማክበር በምዕራብ አርሲ ዞን ዝግጅት እየተረገ መሆኑ ተገለጸ።
የምዕራብ አርሲ ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ከአባ ገዳዎችና ማህበረሰቡ ጋር የበዓሉ አከባበር ዝግጅት አካል የሆኑ ውይይት በሻሸመኔ ከተማ አካሄዷል።
በውይይቱም በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የተውጣጡ አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎች፣ የሀገር ሸማግሌዎች እና ወጣቶች እንዲሁም የበዓሉ አስተባባሪዎች ኮሚቴ ተሳታፊ ሆነዋል።
የበዓሉን ቅድመ ዝግጅትና እንዲሁም ሊደረጉ በሚገቡና ጥንቃቄዎች ዙሪያ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል።
ከወይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ሃዳ ሰንቄ ወይዘሮ ጊርጃ አኖታ፤ የኦሮሞ ህዝብ መገለጫ የሆነውን የእሬቻ በዓል ዘንድሮ ስናከብር ሀገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በደንብ በመገንዘብ መሆን አለበት ነው ያሉት።
ይህም በአካባቢያችን ፀጉረ ልውጥ የሆኑ ግለሰቦችን ካየን ለመንግስት የፀጥታ አካላት መጠቆምና ከኮሮና ጥንቃቄ እያደረግን ማክበር ይኖርብናል ብለዋል።
የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላቶች የጥፋት ዓላማ ለማክሸፍ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባም ነው ሃደ ሲንቄዋ መልእክታቸውን ያስተላለፉት።
መንግሥትም የህዝቡን ደህንነት እና ሰላም ለማስከበር በበዓሉ ዕለትም ሆነ በቅድመ ዝግጅቱ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባውም እንዲሁ።
አባ ገዳ ብርመጂ አቶ ኑጉሴ ገመቹ በበኩላቸው፤ በአካባቢያችን የሽብርተኞች አስተሳሰብ እንዳይስፋፋ በምንችለው አቅም በመዋጋት የእሬቻ በዓልን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ልናከብር ይገባል ብለዋል።
የሰላም አደናቃፊ የሆኑ ግለሰቦችንም ለፀጥታ አካላት በአስቸኳይ ልንጠቁም ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
የሻሽመኔ ወረዳ ባህል እና ቱረዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ጠጅቱ ገለቶ እንደገለጹት፤ ዘንድሮ የእሬቻ በዓልን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ከወዱ ለመዘጋጀት በቂ ውይይት ተደርጓል።
በበዓሉ ዕለትም ሆነ ዋዜማው ላይ ታዳሚው ማህበረሰብ አካባቢውን ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ሊጠብቅ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የእሬቻ በዓል የምናከብረው ዓመት በመጣ ቁጥር ለመሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በዓሉን እንደ አንዱ ገዳ ስርዓት በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብና ባህላችንን የበለጠ ለዓለም ለማሳየት ነው ያሉት ደግሞ የምዕራብ አርሲ ዞን ባህልና ቱረዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ማሊያ ቱፋ ናቸው።
የምዕራብ አርሲ ዋና አስተዳደር አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው፤ የእሬቻ በዓል በአሮሞ ማህበረሰብ ዘንድ ክረምቱ በሰላም ወጥቶ ፀደይን ሲመጣ ፈጣሪን ለማመስገን የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል።
የዘንድሮን የእሬቻ በዓልን ስናከብርም ሀገራችን አሁን ያለችበት የሰላም ጉዳይ እያሰበን ሁሉም ኢትዮዮጵዊ ለሀገሩ ሰላምና ነፃነት በመታገል መሆን አለበት ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደአጠቃላይ የኦሮሞ ማንነት መገለጫ ሆኖ የቆየው የእሬቻ በዓል መስከረም 22/2014ዓ.ም በአዲስ አበባ(ሆረ ፊንፊኔ) እና መስከረም 23 ደግሞ ቢሾፍቱ ( ሆረ አርሰዲ)በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበር ይጠበቃል።