ቻይና ለግብርና ምርት እድገት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቃሚነት ልታጠናክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ለግብርና ምርት እድገት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቃሚነት ልታጠናክር ነው
መስከረም 9 /2014 (ኢዜአ) ቻይና በግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ምርት ለማስመዝገብ የግብርና ሳይንስ ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቃሚነት ልታጠናክር መሆኑ ተገለጸ።
የቻይና የግብርና ሳይንስ አካዳሚ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ 14ኛ ዙር የአምስት አመት የልማት እቅዱን ይፋ አድርጓል።
በእቅዱ መሠረት ቻይና በአምስት አመት ውስጥ የምግብ ደህንነትን ለማስጠበቅ፣ ለመሬት ጥበቃ፣ በሽታን ለመከላከል፣ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግና በጥናትና ምርምር የታገዙ የእርሻ ስራዎችን ለማከናወን የግብርና ሳይንስ ቴክኖሎጂዎችን ትጠቀማለች።
እ.ኤ.አ በ2020 ቻይና የግብርና ሳይንስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዘርፉ ለጠቅላላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት 60 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው አስችሏል።
የተለያዩ የምርት አይነቶች እድገትም 96 በመቶ እንዲያድግ ሳይንስና ቴክኖሎጂው የላቀ ሚና ነበረው ተብሏል።
“ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለቻይና ግብርና ዘርፍ ኢኮኖሚ ማደግ ቁልፍ ሚና አላቸው” ሲሉ የቻይና የግብርና ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት ታንግ ሁዋጁን መግለጻቸውን የዘገበው ሲጂቲኤን ነው።
ወደፊትም በዘረመል ምርምር፣ በምርት እድገት፣ በበሽታ መከላከልና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማበልጸግ የግብርናው ዘርፍ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደሚጠናከር አስታውቀዋል።