በአዲስ መንግስት ምስረታ ዋዜማ የአሜሪካ የተናጠል ማዕቀብ ከምን የመነጨ ይሆን? - ከምሁራን አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ መንግስት ምስረታ ዋዜማ የአሜሪካ የተናጠል ማዕቀብ ከምን የመነጨ ይሆን? - ከምሁራን አንደበት
መስከረም 9/2014 (ኢዜአ) በአዲስ መንግስት ምሥረታ ዋዜማ የአሜሪካ የተናጠል ማዕቀብ ከምን የመነጨ ይሆን? ከምሁራን አንደበት።
ከእስካሁኖቹ ምርጫዎች ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የመረጠበት፣ የመራጭ ድምጽ ስለመከበሩም በተፎካካሪ ፓርቲዎች አንደበት ጭምር የተደመጠበት ባለፈው ወርኃ ሰኔ የተካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ነው።
ምርጫውን ዕውቅና ከመንፈግ ጀምሮ ኢትዮጵያ ወደለየት ቀውስና ብጥብጥ ትገባለች ያሉ ምዕራባዊያንና የእነርሱ ሎሌ ሃይላት ፕሮፓጋንዳ ቢነዙም ኢትዮጵያ የራሷን ዘመን ተሻግራ አዲስ መንግስት ለማቋቋም ዋዜማ ላይ ትገኛለች።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድርና አሸባሪው ህወሓት የፈጠረውን ቀውስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫናቸውን ያበረቱ ምዕራባዊያን በአዲሱ መንግስት ምስረታ ዋዜማ ተጨማሪ ጫና ለማድረግ እየታተሩ ነው።
ለአብነትም የሰሞኑ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ዳግም ወደ ጸጥታው ምክር ቤት የመውሰድ ጉዳይ ብሎም የባይደን መንግስት ተናጠላዊ ማዕቀብ ለመጣል ትዕዛዝ ማስተላለፍ ይጠቀሳሉ።
ይህ በመጪው መስከረም 24 መንግስት ለመመስረት ሽርጉድ በምትለው ኢትዮጵያ የሚደረግ ጫና ለሠብዓዊነት ከመቆርቆር የመነጨ አይደለም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ይሞግታሉ።
ይልቁንም እንደ ህወሓት ሎሌ እንጂ ከአሜሪካ ትዕዛዝ ውጭ የምትንቀሳቀስ የአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር ከመሻትና ለሚመሰረተው መንግስትም እውቅና ከመንፈግ የመነጨ ነው ይላሉ።
የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ውብአንተ አያሌው ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲና ዕድገት የምታደርገው ጉዞ ያልጣማቸው ምዕራባዊያን መልከ ብዙ ጫናዎችን የጀመሩት ዛሬ አይደለም ይላሉ።
በተለይም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እንዲጣል የመንግስታቱ ድርጅትና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ በተዘዋዋሪ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ ተናጠላዊ ማዕቀብ ማስቀመጧን ያወሳሉ።
በአዲስ ምርጫ ዋዜማ የተደረገው ማዕቀብ ሙከራ በኢትዮጵያ የሚመሰረተው ሕጋዊ መንግስት አገሪቷን በሚፈለገው መልኩ ሁለንተናዊ ማሻሻል ያካሂዳል ከሚል ስጋት የመነጨ ስለመሆኑም ያምናሉ።
በሌላ በኩል አሸባሪው ትሕነግ እርምጃ ይወሰድበታል በሚል ስጋትና ቡድኑን መልሶ ወደ ስልጣን የማምጣት ግብግብ በማለት ይገልጹታል።
የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህሩ ዶክተር ዘመነወርቅ ዮሐንስ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ሳይቀር የተመሰከረለት ነጻ ምርጫ አካሂዷል ሕጋዊ መንግስትንም ይመሰረታል ይላሉ።
የምዕራባዊያን አባሯ ማስነሳት ጉዳይ የመነጨው እንደ ትህነግ ያለ ተላላኪ መንግሰት ላይመሰረት ይችላል ከሚል ስጋት የመነጨ ስለመሆኑም ያነሳሉ።
አሜሪካ እንደ ህወሓት አይነት የምዕራባዊያንን ፍላጎት የሚያስፈጽም ስርዓት እንዲገነባ እንደሚሹ ጠቁመው፤ አሁንም የሚደረገው ጫና አዲስ ነገር እንዳልሆነ አክለዋል።
በአሜሪካ የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተጣሉት ምጣኔ ህብታዊ፣ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ማዕቀብ በበርካታ አገራት ተሞክሮ መክሸፉን ይልቁንም አገራትን ለቀውስ ሲዳርግ ቆይቷል ብለዋል።
በኢትዮጵያም ይህን በማድረግ አገሪቷን ለመበታተን እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት የአሸባሪውን ህወሓት ወረራና የፈጸማቸውን ግፎች ለመቋቋም እንቀስቃሴ ሲጀምር ምዕራባዊዊያን ጫናቸው እንደሚያገረሽ ገልጸዋል።
በአሜሪካ ብቻ የተደረጉ ተናጠላዊ ማዕቀቦች በኩባ፣ በቻይና፣ በህንድና መሰል አገራትም ተሞክረው ውጤታማ እንዳልነበሩና፤ ጫናውን ተቋቁመው የዘለቁ አገራት መሆናቸውን ለአብነት ይጠቅሳሉ።
የአሸባሪው የህወሓት ቡድንና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ የሚደረገው ጫና ኢትዮያዊያንን ወደ አንድነትና ኅብረት አምጥቷል ያሉት ምሁሩ፤ ይህ ጫናም የሕዝቡን አንድነት ያጠናክራል ይላሉ።
በሌላ በኩል ማዕቀቡ ኢትዮጵያ ራሷን በራሷ ገንብታ ጠንካራ እንደትይሆን ዕድል የሚያመጣ እንደሆነም ነው የገለጹት።
በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግስት ይህን በመገንዘብ አስፈላጊ ስትራቴጂዎችን ነድፎ የሕዝቡን አንድነት አስጠብቆ ለመዝለቅ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ በምዕራባዊያን ያልተፈተነችበት ዘመን እንዳልነበረ የጉራ፣ ጉንደት፣ አድዋ፣ የሁለተኛው ፋሺስት ወረራና የካራማራ ጦርነትን ማሳያ የጠቀሱት ዶክተር ዘመነወርቅ፤ ነገር ግን ሁሉንም ተሻግራቸዋለች ብለዋል።
የምዕራባዊያን ጫናዎች ትናንትም ነበሩ፣ ዛሬም አለ፣ ወደፊትም ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ዶክተር ዘመነወርቅ፤ ከቀደምት ኢትዮጵያዊያን ታሪክ በመነሳት ኢትዮጵያዊነት አንድነትና ሕብረት ጫናዎችን መቋቋም እንጂ መንበርከክ አይገባም ነው ያሉት።
በአፍሪካ ትልቁን ግድብ የምትገነባው ኢትዮጵያ በሕዝቧ ተሳትፎ ብቻ በመገባደድ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ በሕልውና ዘመቻውም እየተደረገ ያለውን ትብብር በማጠናከር ኢትዮጵያ ጫናውን ትወጣዋለች ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪች አገልግሎት ዲን አቶ አለምነው መልካሙም ምዕራባዊያን ጫና በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር ከመሻት የመነጨ እንደመሆኑ፤ ማዕቀቡም ከዚህ የመነጨ ነው ብለዋል።
በተለይም በቅርቡ የሚመሰረተው መንግስት ፍላጎታችንን ለማሳካት ሳንካ ይሆናል በሚል ለማንበርከክና ለማዳከም ከመፈለግ የሚመነጭ ነው በማለት የምሁራኑን ሃሳብ ይጋራሉ።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ጫናውን ለማለፍ በጋራ መቆም፣ መንግስትም አቋሙን ማጽናት እንዳለበት ምሁራን በተለይ የመረጃ ክፍተትን በመሙላት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።