በምስራቅ ጎጃም ዞን የግዕዝ ትምህርት ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን የግዕዝ ትምህርት ሊሰጥ ነው
ደብረ ማርቆስ ፤ መስከረም 8/2014 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃም ዞን በተያዘው የትምህርት ዘመን የግዕዝ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ስለሺ ተመስገን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የተደረገው ዝግጅት የግዕዝ ትምህርት እንደሌሎች የትምህርት ዓይነቶች በመደበኛነት ለመስጠት ነው።
ዘንድሮ ትምህርቱ የሚሰጠው በጎዛምን እና ደብረኤሊያስ አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤቶች መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ትምህርቱን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
"የመማር ማስተማር ስራውን ስኬታማ ለማድረግ ደረጃውን የሚመጥን የመማሪያ መጻህፍት እና መምህራን እንዲሟሉ ተደርጓል" ብለዋል።
ግዕዝ ቀደምት የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ቋንቋው በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው በአብያተ ክስርቲያናት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል።
አቶ ስለሺ እንዳሉት ፤ የትምህርቱ መስፋፋት ተተኪው ትውልድ የነበረውን ነባራዊ ታሪክ፣ እውቀት እና ጥበብ እንዲረዳ ያግዛል።
"ትምህርት መሰጠቱ በቋንቋው ተከትበው የተቀመጡ በርካታ የብራና እና ሌሎች የግዝ መጻህፍት የያዟቸው እውቀቶችን እና ጥበቦችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ለማዋል ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል" ሲሉም አክለዋል።
እየተዳከመ የመጣውን የግዕዝ ቋንቋ ትንሳኤ ለመመለስ ሲባል ትምህርቱ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ መወሰኑንም ተናግረዋል።
በሁለቱ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠውን የግዕዝ ትምህርት ተሞክሮ በማጠናከር በቀጣይ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ትምህርቱ እንዲስፋፋ የሚደረግ መሆኑንም አቶ ስለሺ አስታውቀዋል።በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ከ83 ሺህ በላይ ህጻናትን በአዲስ ተቀብሎ ለማስተማር ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል።
ለዚህም ከመስከረም 3/ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ህጻናቱን የመመዝገብ ስራ በንቅናቄ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑን ትምህርት መምሪያ በመረጃ ምንጭነት ጠቅሳ የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘገባለች።