በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በጋራ መታገል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በጋራ መታገል ይገባል
ደሴ መስከረም 8/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የሚደረገውን ጥረት ለማምከን የዜጎቿ የተጠናከረ የጋራ ትግል የሚፈለግበት ወቅት ነው ይላሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን።
ምሁራኑ እንደገለጹት ኢትዮጵያዊያን አሸባሪ ቡድኖችን በማስወገድ የሃገራቸውን ሰላምና እድገት ማስቀጠል የጀመሩት ህግ የማስከበር ትግል ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ጀማል ሰይድ እንደገለጹት አሸባሪው ህውሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከመስራቱም ባለፈ በህዝብ ላይ አሰቃቂ ግፍ እየፈጸመ መሆኑ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ቡድኑን ከማውገዝ ይልቅ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የሚደረገው ጥረት አሳዛኝና ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሸባሪዎች ለግል ጥቅማቸው የሚነዙትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው በኢትዮጵያዊያን ላይ የተለያየ ማዕቀብ እንዲጣል መፈረማቸውም ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነታቸውን ለመድፈር የሚደረግባቸውን ስውር አጀንዳ የመቀበል ታሪክም፤ ሞራልም የለንም” ያሉት አቶ ጀማል ፕሬዚዳንቱ እውነታውን እንዲረዱ በተባበረ መንገድ ማሳየት ይገባል ብለዋል።
ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ እውነታውን በማስረዳት፤ አገሩን በመጠበቅና ጫናውን በመከላከል ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም በሉዓላዊነታችንና በነጻነታችን ላይ የያዘው አቋም የሚደነቅና የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ጠቁመው፤ “ሁላችንም ከመንግስት ጎን መቆምና ማገዝ አለብን” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ለጆ ባይደን የጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ተገቢና ወሳኝ ከመሆኑም ባለፈ የኢትዮጵያን ከፍታና የአባቶቻችን የጀግንነት ታሪክ ያንጸባረቀ በመሆኑ ተደስቻለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ምዕራባውያን እንደ አሻንጉሊት የሚያዝዙት መንግስት ለመመስረት ቢፈልጉም ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አሳልፋ እንደማትሰጥ ከማሳየቷም ባለፈ ለአፍሪካ የድፍረትና ጀግንነት ተምሳሌትነቷን እያሳየች ነው” ብለዋል።
ሌላው የዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ይመር አሊ በበኩላቸው እንደተናገሩት አሸባሪው ህወሃት እድሜ ልኩን በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈፀመው ግፍና መከራ አልበቃው ብሎ አሁንም የጥፋት ጥጉን ጦርነት ከፍቶ ዜጎችን እያሰቃየ ነው።
ይሁን እንጂ ለዲሞክራሲ ቆመናል የሚሉ ምዕራባዊያን የሽብር ቡድኑን በመደገፍ ጥፋቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል እያገዙ መሆኑ ያሳዝናል ያሉት መምህሩ ይሄም ዓለም ላይ ያለው የተሳሳተ የይስሙላ የዴሞክራሲ አተገባበር አንዱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለውስጥ ተላላኪ ባንዳ ቀርቶ ለውጭ ጠላትም የማትንበረከክ መሆኗን አባቶቻችን በአደዋና በሌሎችም አጋጣሚዎች በከፈሉት የጀግንነት መስዋዕትነት አሳይተውናል ብለዋል።
የአማሪካ መንግስትና ደጋፊዎቹ ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ሊያነሱ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊያን ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅ የማይከፍሉት መስዋዕትነት እንደሌለም አስረድተዋል።
“ኢትዮጵያን ወደ ሚፈልጉት ስርዓት ለመጠምዘዝና ለማንበርከክ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ማዕቀብ እንዲጣል መፈረማቸው እውነታውን ያላገናዘብና ወደ ሽብር ቡድኑ ያደሉ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል” ብለዋል።
“በዚህም እውነታውን በመረዳት ሊያነሱ እንደሚገባ አመልክተው፤ ኢትዮጵያም ይሔንን ለመቀልበስ ከወዳጅ ሃገራት ጋር መስራት ይገባል” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ አሸባሪውን ቡድን ዳግም ስጋት በማይሆን መልኩ ከመቅበር ጎን ለጎን የውጭ ጫናውና ጣልቃ ገብነቱን ለመከላከል ከመንግስት ጎን የምንቆምበት ወቅቱ አሁን ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጻፉት ግልጽ ደብዳቤም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት ከማሳየቱም ባለፈ የኢትዮጵያውያን አንበርከክም ባይነትን ያሳየ እንደሆነ ገልፀዋል።
በዚህም የሽብር ቡድኑን ወደ ስልጣን እናመጣለን የሚሉ ተላላኪዎችን ያስደነገጠና ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግ ውሳኔ እንደሆነም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማስቀጠል ወጣቱ መከላከያ እና ልዩ ኃይሎችን መቀላቀልና ጠላትን ማሳፈር እንደሚገባምም ምሁራኑ ጨምረው አሳስበዋል።