ቀጥታ፡

ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በመቀየር ለአገራቸው ብልጽግና ሚናቸውን መወጣት አለባቸው

መስከረም 8/2014 (ኢዜአ) ተመራቂ ተማሪዎች ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ልማት በመቀየር አገራቸውን ወደ ብልጽግና ጎዳና ማሻገር እንደሚገባቸው ተገለጸ።

የአድማስ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከ 10ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።

ከተመረቁት ተማሪዎች መካከልም 1 ሺህ 532 በሁለተኛ ዲግሪ፣ 3 ሺህ 919 በመጀመሪያ ዲግሪ እና 4 ሺህ 938 በቴክኒክና ሙያ ይገኙበታል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎቹ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ በኮምፒዩተር ሳይንስ፣ በግብርና ኢኮኖሚ እና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በሌብል፣ በመደበኛና በርቀት ሲማሩ የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሞላ ፀጋዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ለበርካታ ዓመታት ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር አገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ኃይል በማፍራት የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው የመክፈል አቅም የሌላቸውን ከ100 በላይ ተማሪዎች  ነጻ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት ጎን ለጎን ጥናትና ምርምር በማድረግና አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠትም  ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአገር ውስጥ፣  ከውጭ በሚገኙ ቅርጫፎች እና ከዩኒቨርሲቲው ማህረሰብ ጋር በመሆን ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፍ በማድረግ በአገር ልማት ላይ እየተሳተፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድና  ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው፤ አገራችን የገጠማትን ችግር ለማለፍ ዘመኑን የዋጀ የተማረ የሰው ኃይል የምትፈልግበት ወቅት ላይ ናት ብለዋል፡፡

በዚህም ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር አገራቸውን ማገልገልና ወደ ብልጽግና ጎዳና ማሻገር  እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በማዕድንና በቱሪዝም ሀብት የታደለች መሆኗን የገለጹት ኢንጂነር መላኩ፤ ተመራቂ ተማሪዎች ይህንን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር አገራቸውን ማበልጸግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች መመረቅ ብቻ ግብ አለመሆኑን ተረድተው፤ በቀጣይ አገራቸው በምትፈልግባቸው ዘርፍ  ሁሉ ንቁ ተሳታፊ  በመሆን ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የአድማስ ዩኒቨርሲቲም አገራችን የምታደርገውን የእድገት ጉዞ ለማፋጠን የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል በአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ የሆነችው ጠሂር አሰፋ ከተማረችበት ትምህርት ባለፈም በማንኛውም መስክ በመሥራት አገሯን ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡

ተማሪዎች ዓላማቸውን ለሚያደናቅፉ ተግባራት ጆሮ ሳይሰጡ ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚገባቸውም መክራለች፡፡

ከተመረቁት ተማሪዎች መካከልም  67 በመቶ ሴቶች መሆናቸው በእለቱ ተጠቅሷል፡፡

አድማስ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 22 ዓመታት በመደበኛና በርቀት ትምህርት በድህረ-ምረቃ፣ በዲግሪ  በዲፕሎማ እና በሰርቲፊኬት ከ80 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም