ቀጥታ፡

የአሜሪካና ኢትዮጵያ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እሰራለሁ- ካረን ባስ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካና ኢትዮጵያ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚሰሩ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የሆኑትን ካረን ባስና ሳራ ጃኮፕስን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩና የኮንግረስ አባላቱ በዋንኛነት በሰሜን የአገሪቷ ክፍል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምክክር እንዳደረጉ ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።

መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዴት ሊገባ እንደቻለና የዘመቻውን አስፈላጊነት በተመለከተ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዝርዝር ማብራሪያ እንደሰጡ ተናግረዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሀገራዊ ለውጡ ከተጀመረ አንስቶ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር ሲሰራ መቆቱን ለኮንግረስ አባላቱ እንዳብራሩላቸውም ነው የተናገሩት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሸባሪ ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የህግ ማስከበር እርምጃው በምን መልኩ ሲከናወን እንደነበር ማብራሪያ መስጠታቸውንም ነው ያነሱት።

አሸባሪ ቡድኑ መንግስት ያስቀመጠውን የተናጥል ተኩስ አቁም ወደ ጎን በመተው በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ወረራ መፈጸሙንና በዚህም በአካባቢው ከፍተኛ ችግር መፍጠሩን ለኮንግረስ አባላቱ ገለጻ እንደተደረገላቸውም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አውስተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግስት ከመጀመሪያው አንስቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁንም ተመሳሳይ አቋም እንዳለው መናገራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

ነገር ግን ሰላማዊ ሂደቱ በምን አይነት ሁኔታ መተግበር እንደሚቻል ለኮንግረስ አባላቱ በዝርዝር ማስረዳታቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ በበኩላቸው "የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት ችግር ውስጥ እንዲገባ አይፈልግም" ማለታቸውን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

የአሜሪካ ፍላጎት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ጠንካራ ወዳጅነት ይበልጥ መጠናከር መሆኑን ለሚኒስትሩ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት ካረን ባስና ሳራ ጃኮፕስን ያደረጉት ውይይት በመግባባት መንፈስ የተጠናቀቀ  ነው ማለት እንደሚቻል ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

የአሜሪካ ኮንግረስ አባላቱ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።

የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ከሆኑት ካረን ባስ በኮንግረንሱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ስር የአፍሪካ፣ዓለም አቀፍ ጤና እና ሰብዓዊ መብት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው።

በተጨማሪ የጥቁር አሜሪካውያን ኮንግረስ አባላት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ ሳራ ጃኮፕስ ደግሞ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጣር ከ2020 ጀምሮ የኮንግረሱ አባል ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም