የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለው አካሄድ በሀገር ውስጥ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለው አካሄድ በሀገር ውስጥ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለው አካሄድ በሀገር ውስጥ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ መሆኑን የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አባላት ተናገሩ፡፡
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን "በትግራይ ጦርነት ተሳታፊዎች ላይ ያነጣጠረ" በሚል አዲስ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ የፈረሙ ሲሆን፤ ይህም በዋናነት የአሸባሪውን ህወሃት ህልውና ለማራዘም ዓላማ ያደረገ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ቁጣቸውን እየገለጹ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጉዳዩን አስመልክቶ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ "አሜሪካ ኢትዮጵያን በሚመለከት እያራመደች ያለው ፖሊሲ ከአገሬ ፍላጎት ጋር የሚቃረን ከመሆኑም በተጨማሪ ለዚህች ታላቅ አገር ትንግርት ከመሆኑም ባለፈ ጉዳዩ ከሰብዓዊ መብት ጉዳይነት ያለፈ ሆኖ አግኝተነዋል፤" ሲሉ ገልጸዋል።
የአሀዱ ሬዲዩና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር አባል የሆኑት አቶ ጥበቡ በለጠ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤በጆ ባይደን አስተዳደር የወጣዉ ማእቀብ ማዘዣ ፍጹም ተገቢ ያልሆነና በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ የካደ ነው።
የፕሬዝዳን ጆ ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እየተከተለ ያለውን አካሄድ በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ያስተላለፉት መልዕክት ተገቢ እና አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሃት ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ግፍ ሲፈጽም መቆየቱን ገልጸው፤ የጆ ባይደን አስተዳደር ይህን ጉዳይ ለመሸፋፈን የሚያደርገው ጥረት የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነትን የሚያሻክር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በጋራ በመሆን አሸባሪ ቡድኑ የደቀነውን የህልውና ስጋት ለመመከት እየሰሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የጆ ባይደን አስተዳደር በዚህን ወቅት አሸባሪ ቡድኑን ለማዳን የሚያደርገው እንቅስቃሴ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ታሪክ ውስጥ መጥፎ ጠባሳን ለትውልድ ጥሎ ሊያልፍ እንደሚችልም አስረድተዋል።
አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያን ህልውና ከማይፈልጉ የውጭ ሃይሎች ጋር በመሆን "ኑ ኢትዮጵያን እናፍርስ" የሚል መልዕክት በይፋ እያስተላለፈ መሆኑን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሊገነዘብ እንደሚገባም ነው ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ የገለጸው።
በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የቀድሞ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው የአማራና አፋር ክልሎች በየትኛውም ዓለም ያልታየ ግፍ መፈጸሙን ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ ሰላማዊ ዜጎችን ከመጨፍጨፍ ባሻገር የእምነት ተቋማትን በከባድ መሳሪያ አውድሟል፤ እንስሳትን ሳይቀር ገድሏል ነው ያሉት።
በመሆኑም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ያስተላለፈው ውሳኔ ይህን ሃቅ የካደና እጅግ የሚያሳዝን መሆኑን ተናግረዋል።
ውሳኔው ረዥም ዘመናት ያስቆጠረውን የአሜሪካና ኢትዮጵያ ግንኙነት የማይመጥን መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ላይ እየተደረገ ባለው ጫና ይበልጥ አንድ ሆነዋል፤ ይህም አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በአሸናፊነት መንፈስ ሃላፊነቱን እንዲረከብ ያግዘዋል ሲሉም ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ በድል እንደምትሻገር ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
ሌላኛው የማህበሩ አባል እና ደራሲና አዘጋጅ ተስፋየ ማሞ፤ የጆ ባይደን አስተዳደር እየተከተለ ያለው አካሄድ የኢትዮጵያ የፖሊሲ ነጻነት የሚጋፋ መሆኑን ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ በረሷ አቅም ለማደግ በምታደርገውን ጥረት ላይ እንቅፋት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለው እንደሚገነዘቡም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በጉዳዩ ላይ ከአንድ ሉዓላዊ ሀገር የሚጠበቅ ምላሽ ሰጥተዋል ነው ያሉት።
"ኢትዮጵያውያን አንደ ቀደምት አባቶቻችን አንድነታችን በማጠናከር በሁሉም መስክ ሀገራችንን ነቅተን መጠበቅ አለብን፤ ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ ናት" ብለዋል።