ቀጥታ፡

"ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር ነጻነታችንን ለማሳጣት የሚደረግን የውጭ ጣልቃገብነት መመከት ይገባል"

አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር ነጻነታችንን ለማሳጣት የሚደረግን የውጭ ጣልቃገብነት መመከት እንደሚገባ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጅ ምሁራን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አራዳ ክፍል ከተማ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጅ ምሁራን የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሄደዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሐና የሺንጉስ በዚህን ወቅት የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ እኩልነትና ፍትሀዊነት እንዲሰፍን ዋጋ የከፈለ ህዝብ መሆኑን ተናግረዋል።

ነገር ግን አሸባሪው ህወሃት የአማራ ህዝብን ጨቋኝና በዳይ አድርጎ የተሳሳተ ትርክት በማሰራጨት በማንነቱ እንዲሸማቀቅ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ኢትዮጵያውያን ወንድማማች ህዝቦችን በመከፋፈል ኢትዮጵያን ሲዘርፍ መቆየቱን ገልጸው፤ ይህ አልበቃ ብሎት አሁን ላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን በአድነት በመቆም የአሸባሪውን ህወሃት ሀገር የማፍረስ ተግባር እያከሸፉት እንደሚገኙም ነው ያስረዱት።

"አሸባሪ ቡድኑን በአጭር ጊዜ ከእነ አስተሳሰቡ በመቅበር መላው የኢትዮጵያን ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ልማት ማድረግ አለባቸው" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ማናዬ ዘገየ በበኩላቸው አሸባሪው ህሓወት ከምስረታው ጀምሮ የአማራን ህዘብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በሰላም እንዳይኖርና በጥርጣሬ እንዲታይ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል።

በአማራ ህዝብ ላይ ያዘጋጀውን የሃሰት ትርክት በሰነድ አስደግፎ በመተገበር አማራን በማንነቱ እንዲሸማቀቅና አንገቱን እንዲደፋ ከፍተኛ በደል ሲፈጸም መቆየቱንም ነው የገለጹት።

አሸባሪ ቡድኑ አሁን ላይ በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ህጻናትና ሴቶችን በመገድል እንዲሁም  አስገድዶ በመድፈር ለአማራ ህዝብ ያለውን ጥላቻ በግልጽ እያሳየ ነው ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ሀገሩን የሚወድ መሪ ማግኘቷ የኢትዮጵያ ጠላቶችን እንቅልፍ ነስቷቸዋል፤ የውጭ ጫናው የበረታውም ለዚህ ነው" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰላማዊት ጠብቀው ናቸው።

በአፍሪካ በሚነሱ ሀገር ወዳድ መሪዎች ላይ የተለያዩ ጫናዎችና ማዕቀቦች በመጣል ማዳከም የተለመደ አካሄድ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በመሆኑም "ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር ነጻነታችንን ለማሳጣት የሚደረግን የውጭ ጣልቃገብነት መመከት አለብን" ብለዋል።

የውጭ ጠላቶች በሀገር ውስጥ የሚገኙ ባንዳዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማዳከም እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያውያን ይህን በመገንዘብ ለሀገራቸው ህልውና በጋራ መቆም እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት ሙያ መስክ ቅድሚያ ህዝብና ሀገርን በማስቀደም ሃላፊነቱን መወጣት አለበትም ጨምረው ገልጸዋል።


የጉባኤው ተካፋዮች ለኢትዮጵያን ህልውና መጠበቅ እየተዋደቁ ለሚገኙ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት እንዲሁም በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የበኩላቸው ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም