ዓለም አቀፍ ተቋማት ህወሓት እያደረሰ ያለውን ጉዳት በቸልታ በማለፍ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ተቋማት ህወሓት እያደረሰ ያለውን ጉዳት በቸልታ በማለፍ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን የህወሓት አሸባሪ ቡድን በአገርና በንጹሃን ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍና በደል ወደጎን በመተው፤ ቡድኑ የተገፋ በማስመሰል ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ምክትል ከንቲባዋን ጨምሮ የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ አባላት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት" ንቅናቄን ተቀላቅለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ወጣቶች የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማሳወቅ የጀመሩት ንቅናቄ የሚበረታታና የሚደነቅ ነው።
ኢትዮጵያ በርካታ እውነቶች ቢኖሯትም ዓለም አቀፍ ተቋማትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ነባራዊ ሁኔታዋንና በገሃድ የሚታየውን ገጽታ በማዛባት ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የህወሓት አሸባሪ ቡድን ለዘመናት በአገሪቷ ላይ ችግሮችን ሲፈጥር፤ ባለፉት ዓመታትም የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨቆን ግፍና በደል ሲያደርስ መኖሩን አንስተዋል።
"ቡድኑ ስልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ የሕዝብ ጥያቄን ሲያዳፍን፤ በተለይም ወጣቱ ለችግሮች ምላሽ ሲጠይቅ ለጠበንጃ አፈሙዝ ሲዳርግ ነበር" ብለዋል።
ምክትል ከንቲባዋ ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ በሕግ ጥላ ስር በሚገኙ ታራሚዎች ላይም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ረገጣ ስለማድረሱ ተጨባጭ መረጃዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።
ሕዝቡ ይህን የከፋ በደል መሸከም ባለመቻሉም ባካሔደው ትግል ቡድኑን ከስልጣን ቢያስወግደውም አሁንም ኢትዮጵያዊያንን እርስ በእርስ በማጋጨት፣ በማፈናቀልና በመግደል ተግባር መጠመዱን ነው ያወሱት።
ይሁንና ዓለምአቀፍ ተቋማት ይህን የቡድኑን ተግባር ወደጎን ትተው ቡድኑ በደል እንደደረሰበት በማስመሰል ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የማይገናኙ መረጃዎችን እያሰራጩ ነው ብለዋል ገልፀዋል።
እነዚህ አካላት ለቡድኑ ድጋፍ ሲሰጡ የሚታይ ሲሆን በተቃራኒው ኢትዮጵያ ላይ ጫና በማሳደር ስራ ተጠምደዋል ብለዋል።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን እውነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳወቅና ሚዛናዊ ዳኝነት ለማግኘት በወጣቶች የተጀመረው ንቅናቄ ታሪክ የማይረሳውና የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ-መንግስት ብሔራዊ ንቅናቄ አስተባባሪ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ደስታ ሆን ተብሎና በተሳሳተ መረጃ የኢትዮጵያ እውነታ እንዲደበቅ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በወጣቶች የተጀመረው ንቅናቄ 21ኛው ክፍለ ዘመንን የሚመጥን የዲፕሎማሲና የሚዲያ ዓለም አቀፍ ዘመቻ መሆኑን ጠቁመዋል።