ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ቀናዒ ሆኖ በመስራት የገጠሙንን ችግሮች በጋራ ልንሻገር ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ለኢትዮጵያ ቀናዒ ሆኖ በመስራት አሁን የገጠሙንን ችግሮች በጋራ ልንሻገር ይገባል ሲሉ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችና አመራሮች ገለጹ።

አሸባሪው ህወሓት በጥቅምት 24 ቀን 2013 የጀመረውን ጥቃትና አገር የማፍረስ እኩይ ሴራውን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በሠላማዊ ዜጎች ላይ እየፈጸመ ባለው ግፍ ቀጥሎበታል።

በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችና አመራሮችም ይህን የቡድኑን ጥፋትና የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማሳወቅ የተጀመረውን "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ-መንግሥት" ንቅናቄ ተቀላቅለዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር የገጠመንን ፈተና ለመሻገር ከመላው የኢትዮጵያ ወንድምና እህቶቻችን ጋር በጋራ እንቆማለን ሲሉ ነው ለኢዜአ የገለጹት።

"የትግራይን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ" በሚል የሐሰት ትርክት ወጣቱን ለጦርነት እየገበረ ያለው የህወሓት የሽብር ቡድን "የትግራይን ሕዝብ እንደ ማስያዣ የሚጠቀሙበት ጊዜ አብቅቷል" ብለዋል።

መላው የትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊነቱን አጽንቶና ለኢትዮጵያ ቀናዒ ሆኖ እንደሚቆምም ገልጸዋል።

የነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ-መንግሥት ንቅናቄ ኢትዮጵያን ሊመጣባት ከሚችለው ጫና ለማዳን አንዱ መንገድ በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል።

የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ለማሳረፍ የሚያደርጉት ትግል በግልጽ የሚታይ መሆኑን በማንሳት፤ ወደ ትግራይ የገቡ የእርዳታ እህል ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከትግራይ አለመመለሳቸውን እያወቁ ዝምታን መምረጣቸውን እንደ ማሳያ ጠቅሰዋል።

ከዚህም አልፎ በአማራና በአፋር ክልሎች እየተደረጉ ያሉ ወረራዎችን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል ጫና ለመፍጠር የሄዱበት ርቀት እንደሌለ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና በመፍጠር አገሪቷ ጠንካራ ሕዝብና መንግሥት እንዳይኖራት እየሰሩ በመሆኑ፤ ይህን ለመመከት "ሕዝቡ በአንድነት መቆም ይገባዋል" ብለዋል።

አቶ ነጋሽ ወንድማገኝ በበኩላቸው፤ የውጭ ኃይላት "በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት እንደ ትግራይ ተወላጅ እናወግዛለን" ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ "በኢትዮጵያ ድርድር አያውቅም፤ የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያን ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር ሆኖ የመሰረታት በመሆኑ አሸባሪው ቡድን እየሰራ ያለውን እኩይ ተግባር እናወግዛለን" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም