ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር መረባረብ ይገባናል

ሀዋሳ፤መስከረም 8/2014(ኢዜአ) በርካታ ተግዳሮት ታልፎ የመጣውን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በማጠናከር የብልጽግና ጉዟችን ስኬታማ እንዲሆን መረባረብ ይገባናል ሲሉ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።

 ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር በተለያየ የሙያ መስክ ያሰለጠናቸውን ከ6 ሺህ 800 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት በክብር እንግድነት የተገኙት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት ንግግር፤ተመራቂዎች ወደ ስራ ዓለም በመቀላቀል ያስተማራቸውን ህዝብና ሀገር ለማገልገል መዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

"የዛሬ ተመራቂዎች የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መፈጸሙና በሀገሪቱ ህልውና ላይ በአሸባሪው ህወሀት የተከፈተውን ጦርነት በአንድነት እያከሰምን ያለንበት ወቅት በመሆኑ ልዩ ያደርጋችኋል" ነው ያሉት።

"ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትበቃ ናት" ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ሀብቷን በአግባቡ ለመጠቀም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን እውን ለማድረግ አሁን ላይ ብዙ ፈተናዎችን እያሸነፈ እየለመለመ የመጣውን ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር ሁሉም በየተሰማራበት የድርሻውን በመወጣት የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግስት ከፍተኛ ሃብት በመመደብና ምቹ የትምህርት ፖሊሲ በመቅረጽ የሀገሪቱን የዕድገት ጎዳና በምርምር የታገዘ ለማድረግ እያካሄደ ያለውን ጥረት ተመራቂዎች ጠንካራ የስራ ባህል በመፍጠር ማገዝ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ለዚህም ተመራቂዎቹ ግልጽ የሆነ ራዕይ፣ መልካም ስነ ምግባርና ትጋትን በህይወታቸው ማበልጸግ እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በሀገራዊ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማከናወን በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህ እንዲረዳ የመምህራንን አቅም ለማሳደግ በመምህራን ልማት ከፍተኛ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት።

ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ለምርምር ተብሎ የተመረጠው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ የልማት ግብ አስፈላጊውን ሚና ለመጫወት የሚረዳ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ላቀ የምርምር ደረጃ ለማሳደግ በተለያየ መስክ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ዶክተር አያኖ ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በሃገሪቱ ባልተፈለገ መልኩ የተዘራው ልዩነት የፈጠረውን የሰላም እጦትና መሰል ችግሮች በማረም የኢትዮጵያን  አንድነት በመገንባት የብልጽግና ጉዞ  ለማሳካት ተመራቂዎቹ ድርሻቸውን እንድወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኮምፒዩተር ሳይንስ ትምህርት የከፍተኛ ማዕረግ ተመራቂ ናሆም ሙሉጌታ በሰጠው አስተያየት፤ በኮሮና ምክንያት ትምህርት በመቋረጡ ከፍተኛ ጫና ቢፈጥርም ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቅ በመቻሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።

በተመረቀው ሙያ ሀገር በሚትፈልገው ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ መሆኑንም ነው የገለጸው።

በእንስሳት ህክምና በዶክተሬት የተመረቀችው ብርቱካን አበባው በበኩሏ፤ ሀገራችን በርካታ የእንስሳት ሃብት ባለቤት ብትሆንም በዘመነ መልኩ የማይለማ በመሆኑ ውጤታማ አይደለችም ብላለች።

በቆይታዋ ያገኘችውን ትምህርት ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር በማዋሀድ በእንስሳት ሀብት ልማት የተሻለ ውጤት እንዲመጣ የበኩሏን ለመወጣት እንደምትሰራም ተናግራለች።

ዩኒቨርሲቲው ለሲዳማ ቋንቋ፣ ባህልና ሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከተው አርቲስት አዱኛ ዱሞ የክብር ዶክተሬት ድግሪ ሰጥቷል።

አርቲስቱ በወቅቱ እንዳለው ደርግ ሲፈጽም የነበረውን ጭቆና በመቃወም ለስደት ተዳርጎ እንደነበር አስታውሶ፤ለሀገርና ህዝብ መኖር ከሚሰጠው የህሊና እርካታ ባለፈ ይህን መሰል ክብር ያጎናጽፋልም ብሏል።

በማንም ሳትደፈር የኖረችውን የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክቷል።

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች ውስጥ 48 በሶስተኛ ዲግሪ እና ስፔሻሊቲ፣ 799 በሁለተኛ እና  ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ መሆናቸውን በምርቃው ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም