ቀጥታ፡

ወጣቶቹ በአካባቢያቸው የሚመለከቷቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ የስራ ዕድሎችን ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 08 ቀን 2014 (ኢዜአ)  ሥራ ፈጣሪዎቹ ወጣቶች በአካባቢያቸው የሚመለከቷቸውን ችግሮች መፍታት የሚችሉ የስራ ዕድሎችን አስገኝተዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በዲጂታል ስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ 17 ወጣቶች ወደ ስራ መግባት የሚያስችላቸውን የገንዘብ ሽልማት ትናንት አበርክቶላቸዋል።

ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምና ኤክስ ሀብ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ሃሳብን ወደ ሥራ በማበልፀግ ሂደት ለ4 ወራት ያሰለጠናቸውን 17 ወጣቶች ነው የሸለመው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሥራ ፈጣሪ ወጣቶቹ በራሳቸውና በአካባቢያቸው ከተመለከቷቸው ችግሮች በመነሳት ችግር ፈቺ የስራ ዕድሎችን መፍጠር መቻላቸውን ተናግረዋል።

ወጣት ቃልኪዳን ታደሰ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ሳለች ነበር በተማሪዎች የመኝታ ክፍል ውስጥ ያሉ ፍራሾች ተቀዳደውና ተቦጫጭቀው የተመለከተችው።

የፍራሾቹ ሁኔታ ግርምታን ያጫረባት ወጣቷ ምክንያቱን ለማጣራት ስትሞክር አቅም የሌላቸው ሴት ተማሪዎች ለወር አበባ ንጽህና መጠበቂያነት እየተገለገሉበት ስለመሆኑ ትረዳለች።

እናም የእነዚህን ተማሪዎችና የበርካታ ሴቶችን ችግር ለመፍታት በቀላሉ ሊሰራ የሚችል የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ለመስራት በመወሰን ወደ ተግባር እንቅስቃሴ መግባቷን ትገልጻለች።

የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ከምንና እንዴት እንደሚሰራ ለማወቅ ጥረት ያደረገችው ቃልኪዳን  ከፕላስቲክ እንደሚሰራና ለመፈራራስም ከአንድ መቶ ዓመት በላይ እንደሚፈጅበት እንዲሁም በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትልና አካባቢም እንደሚበክል ትገነዘባለች።

ወጣት ቃልኪዳን ከጓደኛዋ ውቢት ታደሰ ጋር በመሆን "ሀፒ ሞዴስ" የተሰኘ ድርጅት በማቋቋም በገበያ ላይ ካለው የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ የተለየና ከኬሚካል የፀዳ፤ በ6 ወራት ሊበሰብስ የሚችል ሞዴስ ለመስራት በቅታለች።

ይህ ስራ ፈጠራ ከሶስት ዓመታት በኋላ ከ6 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግራለች።

እንደ ቃልኪዳን ሁሉ በዙሪያው ከተመለከተው ችግር በመነሳት ህይወትን ቀለል በሚያደርግ ዲጂታል ሥራ ፈጠራ ላይ የተሰማራው ወጣት በረከት ታደሰ ነው።

ወጣት በረከት ቴክኖሎጂ በመጠቀም በበይነ መረብና በሞባይል መተግበሪያ የሚፈልጉትን ምግብ ወይም መጠጥ በማዘዝ ያሉበት ድረስ ማምጣት የሚያስችል የስራ ዕድል ፈጥሯል።

ወጣቱ "አስቤዛ" የተሰኘ ድርጅት በማቋቋም ሰዎች በበይነ መረብ ኦንላይን እና በስልክ መተግበሪያ በመጠቀም መግዛት የሚፈልጉትን እቃ ያሉበት ቦታ ድርስ እንዲመጣላቸው የሚያደርግ ስራ መፍጠር ችሏል።

የሚጣሉ የቁም እንስሳት ቆዳዎችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ቦቃ ሌዘር የተሰኘ ድርጅት ከፍታ ተረፈ ምርቶቹን ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችሉ ስራዎች የሰራችው ደግሞ ወጣት ሕይወት ፀጋዬ ነች።

የተለያዩ ቦርሳና ጫማዎችን በማምረት ለገበያ የምታቀርበው ሕይወት ወጣቶች አካባቢያቸውን በመቃኘት በቀላሉ ስራ መፍጠር እንደሚችሉ ተናግራለች።

የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አማካሪ አቶ በርናንድ ሎራንዶ እነዚህ ወጣቶች ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ችግር ፈቺ መፍትሄ ያመጡ የስራ ዕድሎችን መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

የወጣቶቹ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም ከፍተኛ መሆኑንና በመንግስት በኩልም ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው የገለጹት።

ስራ ፈጣሪዎቹ የአምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሥራ መነሻ ከተበረከተላቸው 17 ወጣቶች መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም