የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቁና በስነ ምግባር የዳበረ አሽከርካሪ ማፍራት ይገባቸዋል- ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቁና በስነ ምግባር የዳበረ አሽከርካሪ ማፍራት ይገባቸዋል- ባለስልጣኑ
አዳማ፤ መስከረም 8/2014 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቁና በስነ ምግባር የዳበረ አሽከርካሪ ማፍራት እንደሚገባቸው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስገነዘበ።
የትራፊክ ደህነትን ለማረጋገጥና አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን አደጋ ለመቀነስ የክልል የትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊዎችና የአሽከርከሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ተወካዮች የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ለኢዜአ እንደገለፁት የአሽከርካሪ ማስልጠኛ ተቋማት የማጭበርበር ዋሻ ከመሆን ወጥተው በተቀመጠው መመሪያና ደረጃ መስራት ግዴታቸው ነው።
አብዛኞቹ የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ከመስመር የወጡ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም ስልጠና እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል ።
"በዚህ አካሄድ ተቋማቱ ሙያና ስነ ምግባርን እንዲሁም ህግና ስርዓትን ጠብቆ ከመስራት ይልቅ የማጭበርበር ዋሻ ከመሆን አልፈው ለትራፊክ ደህንነት ቁልፍ ችግር እየሆኑ ይገኛሉ" ብለዋል።
ባለስልጣኑ በ10 ክልሎችና በሁለት የከተማ መስተዳድሮች ባሉ የማሰልጠኛ ተቋማት ባካሄደው ጥናት ችግሮቹን መለየቱን አመልክተዋል ።
በሀገሪቷ ወጥነት ያለው የአሽከርካሪዎች የሙያ ፍቃድ አሰጣጥ ተደራሽ ለማድረግ የ5 ዓመት የአውቶሞቲቪ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ባለስልጣኑ ህጉን፣ መመሪያና የአሰራር ደረጃን ጠብቆ በማይሰሩ የማሰልጠኛ ተቋማት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
በባለስልጣኑ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ቱሉ በበኩላቸው "በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከተገመገሙ 510 የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ የተቀመጠውን ደረጃ አሟልተው የሚሰሩ 66 በመቶ ብቻ ናቸው"።
34 በመቶ የሚሆኑት ከተቀመጠው ዝርዝር አሰራርና መመሪያ በታች የሚሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በግምገማው ውጤት መሰረት የ42 የማሰልጠኛ ተቋማት ፍቃዳቸው ተነጥቆ ሙሉ በሙሉ መታገዳቸውን አስታውቀዋል።
የተግባር ስልጠናን ወደ ጎን በመተው የንድፈ ሃሳብ ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ፣ ከመስመር የወጡ፣ ከደረጃ በታችና አገልግሎት ባቆሙ ተሽከርካሪዎች ስልጠና መስጠት እንዲሁም የሰልጣኝና ተሽከርካሪዎች ጥምርታ በተቋማቱ የሚታዩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን አቶ ታምሩ አመልክተዋል።
"የመድረኩ ዓላማ በአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት የሚታየውን የአሰራር ክፍተት ለማረም ነው" ያሉት ደግሞ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስን ለማ ናቸው።
"ከክልል ክልል ያለውን ተሞክሮ ለማስፋትና ልምድ ቀስመው ከችግሮቹ እንዲወጡ ለማስቻል መድረኩ ተዘጋጅቷል" ብለዋል ።
በቀጣይ አስር ዓመት የትራንስፖርት ዘርፍ ሊመራበት የተዘጋጀ ፎኖተ ካርታ ላይ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ግንዛቤ አግኝተው ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማስቻል ሌላው የመድረኩ አላማ መሆኑን አስታውቀዋል ።
"የመንገድ ትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር አሽከርካሪዎች ቁልፍ ሚና አላቸው" ያሉት አቶ ዮሐንስ የማሰልጠኛ ተቋማት በተሻለ ደረጃ የማብቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ችግር፣ የአሽከርካሪዎች ሙያዊ ብቃት ማነስ፣ የስነ ምግባር ጉድለትና ግዴለሽነት ከማሰልጠኛ ተቋማት የሚመነጩ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።