በድሬዳዋ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ተቋማት ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ተቋማት ተመርቀው ለአገልግሎት በቁ
ድሬዳዋ፣ መስከረም 8/2014 (ኢዜአ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በህዝብ ተሳትፎ ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 20 መሰረተ ልማት ተቋማት ዛሬ ተመርቀው አገልግሎት መስጠት ጀመሩ ።
የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለህልውና ዘመቻው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚያጠናክሩ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በድሬዳዋ ከተማ በማህበራዊ አገልግሎት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል በህዝብና በአስተዳደሩ በጀት የመሰረተ ልማት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
በድሬዳዋ ቀበሌ 09 ውስጥ በ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ ዛሬ ለምረቃና ለአገልግሎት የበቃው መለስተኛ ድልድይም በአስተዳደሩና በነዋሪው ትብብር ከተሰሩ ተቋማት አንዱ ነው፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጎንፉ ሙሲሳ ለኢዜአ እንዳሉት በ2013 በጀት ዓመት የህዝብን መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ሲሰራ ቆይቷል።
በበጀት አመቱ በዘርፉ በተደረገ ጥረት ከ5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት 23 የመሰረተ ልማት ተቋማት ለማከናወን ታቅዶ 20ዎቹ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
ህዝቡ ለመሰረተ ልማት ተቋማቱ ግንባታ በጥሬ ገንዘብና በጉልበት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት መካከል የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች፣ መለስተኛ ድልድዮች፣ የውሃ ቦኖዎች፣ የመንገድ ዳር መብራት፣ ወፍጮ ቤትና ሱቆች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።
ለአገልግሎት በበቁት መሰረተ ልማት ተቋማት ከ30 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በቀጥታ ተጠቃሚ መሆናቸውን አቶ ጎንፋ አስታውቀዋል፡፡
በተቋማቱ የግንባታ ሂደትም ለ1 ሺህ 250 ሰዎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን አመልከተዋል።
እንደ አቶ ጎንፉ ገለጻ የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች በየጊዜው እያደጉ በመምጣታቸው ይህን ፍላጎት ለማሳካት የሃብት ማሰባሰብና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መመሪያ በመዘጋጀቱ ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ ሥራ ይሰራል።
በቀበሌ 09 ዛሬ የተመረቀው መለስተኛ ድልድይ የአካባቢው ነዋሪዎችን የ13 ዓመታት ጥያቄ መመለሱ ተገልጿል።
ድልድዩን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፉአድ ሱጌ እና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሰአዳ አዋሌ ናቸው፡፡
አቶ ፉአድ ሱጌ በወቅቱ ለኢዜአ እንዳሉት ዘንድሮ የህዝቡን መሰረታዊ የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት የተሻለ በጀት በመመደብ ልማቱ ፍትሃዊና ተደራሽ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
በምርቃቱ ላይ የተገኙት ነዋሪዎች በበኩላቸው ለአገር ሉአላዊነትና ህልውና መረጋገጥ የሚያደርጉትን ድጋፍ ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ከእዚህ ጎን ለጎን በአካባቢያቸው ሠላምና ፀጥታ እንዲሁም ልማት ላይ ተሳትፏቸውን እንደሚያጎለብቱ አስታውቀዋል ።
ወይዘሮ ኑኑ ጋቶ "የዓመታት ጥያቄያችን እንዲፈታ ያደረገውን ተሳትፎ የልማት ተቋማቱን በመንከባከብ እንደግመዋለን" ብለዋል፡፡
"ልጆቻችንን የሀገር ሉአላዊነትን ለማስከበር ወደ ግንባር እንደላክን ሁሉ ለአገር መከላከያና ልዩ ኃይል የጀመርነውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰአዳ አሊ ናቸው።