አሸባሪውን ህወሓት በግንባር ለመፋለም መከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ወስነናል--- የምዕራብ ጎንደር ዞን ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪውን ህወሓት በግንባር ለመፋለም መከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ወስነናል--- የምዕራብ ጎንደር ዞን ወጣቶች
መተማ መስከረም 8/2014- (ኢዜአ)-ለሀገርና ለህዝብ ክብር ሲሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት የሆነውን አሸባሪውን ህወሓት በግንባር ለመፋለም መከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል መወሰናቸውን የምዕራብ ጎንደር ዞን ወጣቶች ገለፁ።
ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ሽኝት ተደርጓል።
በቅርቡ በምህንድስና የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ወጣት ዋሲሁን አሊ ለኢዜአ እንዳለው አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስና የሀገር አንድነትን ለማስከበር መከላከያ ሠራዊቱን ለመቀላቀል ወስኗል።
"ጠንካራ ወታደራዊ አቅም የሌላት ሀገር የዜጎቿን ደህንነት ማረጋገጥ አትችልም" ያለው ወጣቱ፣ እስካሁን በማንም ሃያል ያልተደፈረች ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።
ሀገርንና ህዝብን መውደድ እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ መሆን እንዳለበት ጠቅሶ፣ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ መከላከያ ሠራዊትን በመቀላቀሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
ዘመናዊ ሠራዊት ለመገንባት እየተሰራ ባለበት በአሁኑ ወቅት መከላከያን መቀላቀሉ ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለማበርከት ዕድል እንደሚፈጥረለት ገልጿል።
ሌላኛዋ ወጣት ፍሬህይወት ወርቁ በበኩሏ በህልውና ዘመቻው ሴት የመከላከያ ሠራዊት አባላት በጦር ግንባር እየፈጸሙት ባለው አኩሪ ገድል ኩራት እንደሚሰማት ተናግራለች።
አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በግንባር በመፋለም የጀግንነት ታሪክ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።
"የሀገር ዳር ድንበርን በደሙና በአጥንቱ እያስከበረ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት በመቀላቀሌ ታላቅ ክብርና ኩራት ተሰምቶኛል" ስትል ገልጻለች።
"መላ ኢትዮጵያዊያንን ባቀፈ መልኩ በሀገራዊ ስሜት እየተደራጀ ያለውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል በመወሰኔ ደስተኛ ነኝ" ያለው ደግሞ ሌላኛው ምልምል ወጣት ይርሳው አረጋ ነው።
በአሸናፊነት ወኔና ስንቅ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ሽብርተኛው ህወሓትን ለመደምሰስ ከወዲሁ የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረጉን ተናግሯል።
በቀጣይ በስልጠና በሚያገኘው ወታደራዊ እውቀት ሀገሩን በጀግንነትና በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ጠቁሟል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የህዝብ ሰላምና ደህንነት መምሪያ የምልምል መከላከያ ሠራዊት አስተባባሪ አቶ ዮናስ ጋዲሳ በበኩላቸው እንዳሉት የዞኑ ወጣት ያለው የሀገር ፍቅር ስሜት ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆን ነው።
"ከዚህ በፊት የክልሉን ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት ከተቀላቀሉ ወጣቶች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት መንግስት ያደረገውን ጥሪ በመቀበል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዞኑ ወጣት ወደ መከላከያ ሠራዊቱ እየገባ ይገኛል" ብለዋል።
የምዕራብ ጎንደር ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት የሀገር ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባሻገር ልጁን መርቆ ወደ መከላከያ ሠራዊቱ በመሸኘቱ ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ አቶ ዮናስ አስታውቀዋል።