ቀጥታ፡

የሠራዊቱን ገድል ለትውልድ ለማሳወቅ በትኩረት እንሰራለን- የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስፈጻሚዎች

ደባርቅ ፤ መስከረም 8/2013(ኢዜአ) መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ዳር ድንበርና ክብር ለማስጠበቅ እየከፈለ ያለውን መስዋትናትና እየፈፀመ ያለውን የጦር ሜዳ ገድል ለትውልድ ለማሳወቅ በትኩረት እንደሚሰሩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስፈጻሚዎች አስታወቁ።

የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስፈጻሚዎቹ በማይጠብሪ ግንባር አሸባሪውን የህወሃት ቡድን እየደመሰሰ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ጎብኝተዋል።

ከጎብኚዎቹ መካከል የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እንደገለጹት፤ ከጀግናውና አይበገሬው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል መገኘት ኩራትን ያጎናጽፋል።

የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስፈጻሚዎች ሠራዊቱን ግንባር ድረስ ሂደው የጎበኙት ለማየት ብቻ ሳይሆን "የትም፣መቼም፣ በምንም ሠራዊቱ እንዲያሸንፍ ፣ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ስራ ላይ ስለሆንን ነው" ብለዋል።

"አሁን ደግሞ የበለጠ የሞራል ከፍታችን ጨምራችሁታል" ያሉት አቶ ሰይፈ፤ ከሠራዊቱ ጋር ድልን ለማስቀጠል  ይሰራል ነው ያሉት።

''ሠራዊቱ የሀገሪቱ ትልቅ መከታና ጠበቃ ነው'' ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖራሽን  ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ንጉሴ ምትኩ ናቸው።

"አሁን በመጣንበት ግንባር ብቻ ሳይሆን በየቦታው እሳት በተነሳ ቁጥር እየሄዳችሁ የምታበርዱት እናንተ ናችሁ እናከብራችኋለን" በማለት ሠራዊቱን አመስግነዋል።

"እኛ የሚዲያ አካላት ደግሞ የናንተን ጀግንነት ፣ የናንተን የጦር ሜዳ ገድል እንዘክራለን ፣ ከፍ ከፍ እናደርጋለን" ሲሉም ገልጸዋል።

መከላከያ ለሀገሩ የዋለውን ፋይዳና ሚና ለማሳወቅ ሚዲያው ሌት ተቀን ሳይሰለች ይሰራል ነው ያሉት ዶክተር ንጉሴ።

የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ አስራት በበኩላቸው "የአባቶቻችን አንድነት የተማርኩት ከታሪክ መጽሃፍና ከአባቶች የአድዋ ታሪክ ላይ ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።

"ዛሬ በተግባር በዚህ ቦታ ላይ ተገኝቼ ለሀገር አንድነት ልክ እንደ አድዋ የኢትዮጵያ ልጆች የሀገራቸውን ጠላት ለማንበርከክ በጋራ ሲቆሙ ሳይ ኩራት ይሰማኛል" ብለዋል።

"እናንተ በርትታችሁ ታሪክ እየሰራችሁ ነው፤ እኛ ደግሞ እንደ ሚዲያ እውነተኛውን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ዝግጁ ነን" ነው ያሉት አቶ ዝናቡ።

"የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች ግንባር ድረስ መጥተን ሠራዊቱን እየጎበኘን ያለነው ለልጆቻችን ኢትዮጵያ ጀግኖች እንዳሏት፣ ኢትዮጵያ ማንነቷን የማያስደፍሩ አንበሶች እንዷሏት፣ ለመንገር ነው" ያሉት ደግሞ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው።

በተግባር ያየነውም እሱን ነው፤  ከፈጣሪ በታች የኢትዮጵያ ዋና ወኪል የመከላከያ ስራዊት ነው ብለዋል።

የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሜጀር ጀነራል መሰለ መሰረት፤ "ህዝብ የሰጠንን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ሌት ተቀን እየሰራን ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።

የመገናኛ ብዙሃን አመራሮች ግንባር ድረስ ተገኝተው ሠራዊቱን ማበረታታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው"በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብስራት እናሰማለን" ብለዋል።

"ህዝባችን ከጎናችን ነው" ያሉት ሜጀር ጀነራል መሰለ፤ ከዚህ ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰብ እንደ አንድ እናትና አባት ልጅ በጋራ ተግባብቶና ተናቦ ለድል የሚሰራ ሠራዊት  ነው ሲሉም አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም