ቀጥታ፡

ሴት ሚንስትሮች በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ተፈናቀለው ደሴ ከተማ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 08/2014(ኢዜአ) ሴት ሚንስትሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በአሸባሪው የህወሓት ወረራ ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለተጠለሉ ዜጎች ምግብ ነክና ምግብ ያልሆኑ የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ሚንስትሮቹ የንጽህና መጠበቂያና የህፃናት አልሚ ምግብ ጨምሮ ፓስታ፣ ማካሮኒና ሌሎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ነው ለተፈናቃዮቹ ያደረሱት።

ተፈናቃዮቹን ለመጎብኘት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የትራንስፖርት ሚንስትር ዳግማዊት ሞገስ፣ የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ሽታዬ ምናለ፣ ባለሃብቷ ትልቅ-ሰው ገዳሙ እና ሌሎች ከፍተኛ ሴት የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ደሴ ከተማ ተገኝተዋል።

በሴት ሚንስትሮቹ የተመራው የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡድን በሰኞ ገበያ ፩ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ 353 ሺህ 318 ሠብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች በደሴ ተጠልለው እንደሚገኙ ከዞኑ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም