አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ጽኑ አቋም አላት-የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ጽኑ አቋም አላት-የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፤2014 (ኢዜአ) አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ጽኑ አቋም እንዳላት የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የአሜሪካ የኮንግረስ አባል ከሆኑት ካረን ባስ እና ሳራ ጃኮፕስ ጋር ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ውይይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ለአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ግጭት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም አሸባሪው ህወሃት በትግራይ አጎራባች ክልሎች ወረራ በመፈጸም ግጭቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ማስፋቱን ገልጸዋል ነው ያሉት።
መንግስት ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አስታውሰው፤ አሁንም ችግሮች በሰላም እንዲፈቱ ጽኑ አቋም እንዳለው መናገራቸውንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ካረን ባስ በበኩላቸው አሜሪካ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ ጽኑ አቋም እንዳላት መግለጻቸውን ነው ያወሱት።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ጊዜ የቆየ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላትና ይህ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውንም ቃል አቀባዩ አንስተዋል።
የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት እና የምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ውይይት በመግባባት መንፈስ የተካሄደ እንደነበረም አስታውቀዋል።