ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መከበር ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀንነታችን ይቀጥላል

ደሴ፣ መስከረም 8/2014 (ኢዜአ) አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ደምስሶ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት የደጀንነት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያዊያን በአራቱም የአገሪቷ ማዕዘናት ሽብርተኛውን የህወሓት ወራሪ ኃይል ለመደምሰስ ተጋድሎ እያደረገ እየተፋለመ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀንነታቸውን እያሳዩ ይገኛል።

የደሴ ከተማ ወጣቶችና የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትም በወሎ ግንባር ተሰልፎ አሸባሪውን ኃይል በማሳደድ ላይ ለሚገኘው ሠራዊት በግንባሩ በመገኘት አለኝታነታቸውን አሳይተዋል።

የሕዝብ ልጅ ለሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

ሕዝባዊ የደጀንነት ድጋፉ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ በመሆን የሽብር ቡድኑን በያለበት ለማጥፋት ከፍተኛ ተነሳሽነት እየፈጠረም ይገኛል።

የደሴ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ መከተ ዘውዱ፤ የከተማዋ ማኅበረሰብ አደረጃጀቶችን በመፍጠርና በግንባር በመገኘት ለሠራዊቱ ያለውን ደጀንነት በተግባር እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የወሎ ሕዝብ ለአገር መከላከያ ሠራዊቱ አለኝታነቱን አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የ81ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ የደሴ ነዋሪዎች ያደረጉት ድጋፍ ለሠራዊቱ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሚሆነው ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም