የአማራ ምሁራን በአገር ማዳን የሕልውና ዘመቻ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ምሁራን በአገር ማዳን የሕልውና ዘመቻ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013 የአማራ ምሁራን በአገር የማዳን የሕልውና ዘመቻ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያን ለመታደግ እንዲሰለፉ ጥሪ ቀረበ።
የምሥራቅ አማራ ዩኒቨርስቲዎች ምሁራን በደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ በወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ላይ እየመከሩ ነው።
የምክክር መድረኩ እየተካሄደ የሚገኘው የፌዴራልና ክልሎች ባለስልጣን አመራር አባላት በተገኙበት ነው።
የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉሥ ታደሰ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ሕወሃት አማራን በማጥፋት ኢትዮጵያን መበታተን ዓላማው አድርጓል።
አሸባሪ ቡድኑ በገባባቸው የአማራና አፋር አካባቢዎች አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀለኞችን መስራቱን፣ የግፍ ጥግ የሆኑ ድርጊቶችን ሁሉ መፈጸሙን ጠቁመው፤ በዚህም ህዝቡን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መዳረጉን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ለመድፈር የውጭ ኃይሎች ሲመጡ "የውስጥ እፉኝት ልጆች ተባባሪዎች ነበሩ፤ ግን አርበኞች በአንድነት ከጠላትና ባንዳ ጋር ተዋግተው አገር ጠብቀው አስረክበዋል" ብለዋል።
በአሸባሪው ሕወሃት በአማራ ላይ የተፈፀመው ግፍ ተነግሮ የማያልቅ መሆኑን አመልክተው፤ "ምሁራን በሰነድ ማስረጃ አጣቅሰን ለዓለም ማሕበረሰብ ማሳወቅ አለብን" ብለዋል።
የመኖር አለመኖር ጉዳይ በመሆኑ "የቀደምት አባቶች ኢትዮጵያዊነት ወኔ ተላብሰን የተደቀነብንን ሁለንተናዊ የሕልውና አደጋ በጋራ መመከት አለብን" ብለዋል።
የደብረ ብርሐን ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ የፀጥታ አካላት የአንድ ወር ደመወዝና ደም ልገሳ ከማድረግ በተጨማሪ በሁሉም ዘርፍ ከሕልውና ዘመቻው ጎን መሰለፉን አረጋግጠዋል።
ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት አገር በማዳንና የአማራን ልዕልና ለማስጠበቅ በሕልውና ዘመቻ የስራ ስምሪት ወስደው መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ነው ያስረዱት።
የፌዴራል የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፤ አሸባሪውና ከሃዲው ቡድን በተለይም አማራን የጥቃት ማዕከል በማድረግ አገር ለማፍረስ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
"እኔ ካልበላሁ ጭሬ ልድፋው" በሚል ብሂል ከፋፍሎ ለመግዛት አልሳካ ሲለው አገር ለማፍረስ የቻለውን ሁሉ ዕኩይ ተግባር መፈፀሙን ገልፀው፣ "አማራና አፋር ክልሎችን የጥቃት ማዕከል አድርጓል" ብለዋል።
በአማራ ህዝብ ላይ የማይታሰቡና ሰው ሊያደርጋቸው ይችላል የማይባሉ ዕኩይ ግፎች እየፈፀመ መሆኑን አመልክተው፤ "ቡድኑ እስካልጠፋ ድረስ የአማራ ማህበረሰብ ማህበራዊ እረፍት አያገኝም፣ በመሆኑ አማራጩ መኖር ወይ አለመኖር ነው፣ እጣ ፈንታችን በአማራ ማህበረሰብ አንድነትና በኢትዮጵያዊያን ትብብር ነው" ብለዋል።
ለዚህ አንድነት የማምጣትና ማህበረሰብ የማንቃት ጥበብና ችግር የማቃለል አማራጮች ደግሞ ከምሁራን እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
"ባለሀብቱ፣ ነጋዴው፣ ወጣቱ፣ አርሶ አደሩ ሁሉም በየመስኩ እየሰራ ነው" ያሉት አቶ ንጉሱ፤ ምሁራኑን በወቅታዊ የሕልውና ዘመቻ አዋጅ መቀላቀል የምሁራን ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።
"አሸባሪ ቡድኑን ለመቅበር በጋራ መቆምና ያለምንም ልዩነት ከሁሉም ጊዜ በተሻለ መዝመት ይገባል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአሸባሪ ቡድኑ ምሁራን ሲዖል ለመግባት እንደዘመቱት ሁሉ "እኛም ህዝባችንን ለመታደግና አገር ለማዳን ስምሪት ወስደን መነሳት አለብን" ነው ያሉት።