ቀጥታ፡

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ወጣቱ የኢትዮጵያ አለኝታነቱን የሚያሳይበት ዘመቻ ነው

መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ጉዳይ ቅድሚያ በመሰለፍና ሕልውናዋን በማስከበር 'ለአገራቸው አለኝታ እንደሚሆኑ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ገለጹ።

በመዲናዋ የየካ ክፍለ ከተማ ወጣቶች የተሳተፉበት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ንቅናቄ ዘመቻ ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ፣ "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" አስተባባሪዎች፣ ወጣቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅና የህወሓት ቡድን የፈጸማቸውን እኩይ ተግባራት ማጋለጥን ዓላማ ያደረገው ዘመቻ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የየካ ክፍለ ከተማ ወጣቶች ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ ተቀብለው በአገራቸው ጉዳይ ቀድመው በመገኘት አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ ወጣቱ ለኢትዮጵያ አለኝታ መሆኑን የሚያሳይበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘመቻው ወጣቶች የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም በማስረዳት ድምጿ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ እየገጠማት ያለውን ጫና መከላከል እንድትችል ወጣቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በሚካሄዱ ዘመቻዎች ላይ ተሳትፎውን ማሳደግ ይጠበቅበታልም ብለዋል።

የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ተክሌ ነዋሪዎች በ"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ በመሳተፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስከበር እንደሚቆሙ ገልጸዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ አክሊሉ ታደሰ ኢትዮጵያዊያን በዘመቻው በመሳተፍ ነጻነታችንን እናስጠብቃለን፤ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ እንድታመራ ሃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።

"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ዘመቻ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል። 

በ"የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የተጻፉ ደብዳቤዎች እቃዎችን የማጓጓዝ አገልግሎት በሚሰጠው ዓለም አቀፍ ድርጅት ዲኤችኤል አማካኝነት ወደ ዋይት ሐውስ እንደሚላኩም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም