በዲጂታል ስራ ፈጠራ ውድድር ያሸነፉ ወጣቶች የሥራ መጀመሪያ ገንዘብ ተሸለሙ

94

አዲስ አበባ መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በዲጂታል ስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ 17 ወጣቶች ወደ ስራ መግባት የሚያስችላቸውን የገንዘብ ሽልማት አበረከተ።

ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራምና ኤክስ ሀብ ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመተባበር ሃሳብን ወደ ሥራ በማበልፀግ ሂደት ለ4 ወራት ያሰለጠናቸውን 17 ወጣቶች ዛሬ አስመርቋል።

በ2012 ዓ.ም በዲጂታል ንግድ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች ላይ 755 ወጣቶች የንግድ ሃሳብ አቅርበው የመግቢያ መስፈርቱን ያሟሉና ሃሳባቸው የተመረጠ 17 ወጣቶች በተለያዩ መርሐ ግብሮች ስልጠና ወስደዋል።

ወጣቶቹ ምቹ ሁኔታ ቢያገኙ ሊሠሩ በሚያስቡት ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ያገኙ ሲሆን የንግድ ሀሳቦቻቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉበት የገንዘብ ሽልማትም አግኝተዋል።

ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን ጨምሮ በአምራችነት፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በኪነ ጥበብና መዝናኛ ላይ ያተኮሩ የንግድ ሀሳቦችን ነው ወጣቶቹ ያቀረቡት።

ወጣቶቹ አሸናፊ በመሆናቸው የምስክር ወረቀት ያገኙ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም አማካኝነት በተገኘ ገንዘብ ለእያንዳንዳቸው የአምስት ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሥራ መነሻ ተበርክቶላቸዋል።

ዘመኑ የዲጂታል በመሆኑና የኢትዮጵያም ኢኮኖሚ ወደ ዲጂታል ስለሚያመራ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ስራ ፈጣሪዎቹን ወጣቶች እንደሚያበረታታ ኮሚሽነር ንጉሡ ጥላሁን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በአነስተኛ ድጋፍ ለውጤት የሚበቁ ወጣቶችን መደገፉን እንደሚቀጥል የገለፁት አቶ ንጉሱ አሸናፊዎቹ ወጣቶች ዕድሉን ያላገኙ ወጣቶችን በሀሳብ እንዲደግፉና የስራ እድል በመፍጠር ለራሳቸውና ለአገራቸው ይበልጥ የሚጠቅሙ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም