ቀጥታ፡

የደሴ ሕዝብ በወሎ ግንባር ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ማዕድ አጋራ

መስከረም 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደሴ ከተማ ሕዝብ በወሎ ግንባር ተሰልፎ አሸባሪውን የህወሓት ኃይል ለመቅበር ተጋድሎ እያደረገ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት በግንባር ተገኝቶ ማዕድ አጋራ።

ማዕድ ያጋሩት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሰራዊቱ ለሕይወቱ ሳይሳሳ አሸባሪውን ህወሓትን ለመደምሰስ እየተጋደለ ያለ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ገልጸዋል።

“ለዚህ የቁርጥ ቀን ልጅ ማዕድ ማጋራት ሲያንስ እንጂ አይበዛም” ብለዋል።

ሽብርተኛውን ወራሪ ኃይል ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት ለኢትዮጵያ እየተጋ ለሚገኘው የቁርጥ ቀን ልጅ የሚያደርጉትን የደጀንነት ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ማዕድ የተጋሩት የሠራዊቱ አባላት ሽብርተኛውን ወራሪ ኃይል እየደመሰሱ ባሉበት ግንባር ደጀኑ ሕዝብ ያደረገው ድጋፍ የሞራል ስንቅ እየሆናቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብም አሸባሪውን ወራሪ ኃይል እስከመጨረሻው በማጥፋት ሕዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ በወኔና በቁጭት ድባቅ እየመቱት እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በመውጋት ሕዝቧን ለእንግልትና ስቃይ እየዳረገ የሚገኘውን ወራሪ ኃይል ለማጥፋት ያላቸውን ቁርጠኝነትና ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም