ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር በጥናት ተደግፎ ሊሰራ ይገባል

አዲስ አበባ መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር ትውፊቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር በጥናት የተደገፈ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ።

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባባር የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል።    

በውይይቱ ላይ የመስቀል ደመራ በዓል ለሃይማኖታዊ ፋይዳው በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም፣ የኢኮኖሚ ገንዘብ ዝውውር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።

በመድረኩ የበዓሉ አከባበር ማህበራዊ መስተጋብርን ከማጠናከር አኳያ ያለውን ፋይዳ በሚመለከትም ውይይት ተካሄዷል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የመስቀል በዓልን ከሚያደምቁ  ገጽታዎች አንዱ ባህላዊ አልባሳት መሆኑን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ከባህላዊ አልባሳት ይልቅ ቲሸርት ማሳተም ላይ ትኩረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።    

የመስቀል ደመራ በዓል የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ ውበቱ የሚጎላው በጋራ ሲከበር መሆኑን ገልጸው፤ "በአንዳንድ ቦታዎች ግን ከአደባባይ ይልቅ በግል ወደ ማክበር እየተቀየረ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል" ነው ያሉት።    

መስቀል ከማይዳሰስ ቅርስ ውስጥ መካተቱን ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ በዓሉን ለማክበር የሚሰባሰቡ ሰዎች የሚጠቀሟቸው ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ለትውልድ የማስተላለፉ ረገድ በበቂ ሁኔታ አለመሰራቱን አንስተዋል።   

በደቡብ ክልል የዳውሮ ብሔረሰብ የሚጠቀምበት ዚዚና ዲንካ የተባሉ የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎችን የሚጫወቱ ተተኪዎች ቁጥር መቀነሱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ ገጽታው በተጨማሪ ለቱሪዝም ማደግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል። 

በመሆኑም የበዓሉ አከባበር ትውፊቱን ጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው ብለዋል።   

በተለይም የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዳይበረዙ የመከላከሉ ስራ ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በጥናት የተደገፈ ሥራ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። 

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው፤ መስቀል ደመራን ጨምሮ ሌሎች የማይዳሰሱ ቅርሶች በኢትዮጵያ ልማትና ብልጽግና የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም