አሸባሪው ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለፈፀመው ጥቃት በዓለም አቀፍ ህግ በጦር ወንጀለኝነት መጠየቅ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለፈፀመው ጥቃት በዓለም አቀፍ ህግ በጦር ወንጀለኝነት መጠየቅ አለበት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለፈፀመው ጥቃት በዓለም አቀፍ ህግ በጦር ወንጀለኝነት መጠየቅ እንዳለበት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያውያን ጠየቀ።
ጥምረቱ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ጉዳይ በሚመለከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የጥምረቱ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ሽባባው፤ ጥምረቱ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በመፈጸም በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸመውን ጥቃት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ተናግረዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በሀገራችን ሰላማዊ ዜጎች፣በቤተ ክርስቲያንና መስጂዶች፣በትምህርት ቤቶችችና ጤና ጣቢያዎች እየፈጸመ ያለውን ጥቃት አጥብቀው እንደሚያወግዙም እንዲሁ።
በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪ ቡድኑን በይፍ እንዲያወግዘው እንጠይቃለን ብለዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ለፈጸመው ጭፍጭፋ በዓለም አቀፍ ህግ በጦር ወንጀለኝነት ሊጠየቅ ይገባል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀገር ለማፍረስ እያደረገ ያለውን ተግባር በመመከት ረገድ እያሳዩት ያለውን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ጥምረቱ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረስ የሚደረግ የትኛውንም አይነት ጥረት እንደሚቃወምም ነው የገለጹት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረውን ጫና አንቀበልም፣ ጉዳዩም የአፍሪካ ህብረት ማእቀፍ ስር መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል።
ጥምረቱ ሱዳን በወረራ ከያዘችው የኢትዮጵያ ግዛት ለቃ ልትወጣ ይገባል ሲልም አሳስቧል።
አንዳንድ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሀሰት ዘገባ በማሰራጨት በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ የተፈጸመውን የዜጎች እልቂት በኢትዮጵያ ለመድገም ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ መታቀብ እንዳለባቸው ጥምረቱ አስገንዝቧል።