የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የጂቡቲ አቻውን 4 ለ 0 አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የጂቡቲ አቻውን 4 ለ 0 አሸነፈ
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 በታንዛንያ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የጂቡቲ አቻውን 4ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸነፈ። በ2011 ዓ.ም በታንዛንያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሴካፋ ዞንን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በታንዛንያ የማጣሪያ ጨዋታ እየተካሄደ ይገኛል። ዛሬ በቻማዚ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቢኒያም ባንጃ፣ በረከት ካሌብ፣ ምንተስኖት እንድሪያስና ቢኒያም አይተን ጎሎች የጅቡቲ አቻውን 4 ለ 0 መርታት ችሏል። በዚህም መሰረት ብሔራዊ ቡድኑ ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ምድብ አንድን መምራት ችሏል። ቡድኑ ከትናንት በስቲያ በመጀመሪያ ጨዋታው የኡጋንዳ አቻውን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ጨዋታውን ነሐሴ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያደርግ ይሆናል። የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። በታንዛንያ በመጪው ዓመት በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አገሮችን ለመለየት የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።