ቀጥታ፡

አሜሪካ ከ3 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ከትምህርት ገበታ ያስቀረውን የህወሓት አሸባሪ ቡድን ተጠያቂ ማድረግ ጫና ልታደርግ ይገባል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 07/2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት ከ3 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ከትምህርት ገበታቸው ያስቀረውን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ተጠያቂ ለማድረግ ጫና እንዲያደርግ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ጠየቁ።

የትምህርት ሚኒስቴር የአመራር አባላት "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" ንቅናቄን ተቀላቅለዋል።

አመራሮቹ የአሜሪካ መንግስት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና አስተዳደራቸው የኢትዮጵያ ትክክለኛ ነባራዊ እውነታ እንዲደርሳቸው መልዕክታቸው ላይ ፊርማቸውን በማኖር የነጩን ፖስታ ንቅናቄ ተቀላቅለዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ አሸባሪው ቡድን በትምህርትና በሌሎችም መሰረተ ልማቶች ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመትና እውነታውን ለዓለም ለማሳወቅ ንቅናቄውን መቀላቀላቸውን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ አሸባሪው ህወሓት በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልልሎች 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናትን ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲያደርግ በሺህዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶችን አውድሟል።

የሚኒስቴሩ አመራሮች የሚልኩት መልዕክት ድምጻቸውን ከሚያሰሙ ወጣቶች በተጨማሪ ድምጻቸው የማይሰማ በእንባ፣ በለቅሶና በመከራ ውስጥ የሚገኙ የ3 ሚሊዮን ህጻናትን ድምጽ መሆኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በከፈተው ጦርነት ምክንያት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች 10 ሺህ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

በመሆኑም የአሜሪካ መንግስት ህወሓት እየፈጸመ ባለው የሽብር ተግባር በዓለም ተጠያቂ እንዲሆን ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

መስከረም 3 በተጀመረው "የነጩ ፓስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት" ንቅናቄ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉበት ነው።

እስከ መስከረም 15 በሚቆየው ንቅናቄ ወጣቶችን ጨምሮ ከ5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን እውነታና አሸባሪው ህወሓት እያደረሰ ያለውን ጥፋት የያዘውን መልዕክት ፊርማቸውን በማኖር ለአሜሪካ መንግሥትና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ይልካሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም