ባለፉት ስምንት ዓመታት የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ ባደረጉ ተቋማት 3 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳን ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስምንት ዓመታት የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ ባደረጉ ተቋማት 3 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳን ተችሏል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 07/2014 (ኢዜአ) ባለፉት ስምንት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ ባደረጉ ተቋማት 3 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ካይዘን የሃብትና ጊዜ ብክነትን በመቆጠብ ምርታማነትንና የተገልጋይ እርካታን የሚጨምር የአሰራር ፍልስፍና ነው።
በኢትዮጵያም የካይዘን ፍልስፍናን ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ገቢራዊ የሚያደርጉ በርካታ ተቋማት ያሉ ሲሆን፤ ተቋማቱም ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ጉዲሳ የካይዘን የሠራተኞችን የሥራ ፈጠራ በማሳደግ፣ የሚባክን ሃብትና ንብረትን በመቆጠብ እንዲሁም ምርታማና ተወዳዳሪ ተቋማትን መፍጠር ያስችላል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ካይዘን መተግበር ከጀመረ ስምንት ዓመታት እንደተቆጠሩ አስታውሰው፤ በእነዚህ ዓመታት 700 የሚሆኑ የተለያዩ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፍልስፍናውን መተግበራቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ተቋማት መካካል ጠንካራ የአመራር ክትትል ተግባራዊ በተደረገባቸው ላይ የተሻለ ውጤት መመዝገቡንም ነው የገለጹት።
በዚህም 3 ቢሊዮን ብር ከብክነት ማዳን ተችሏል ብለዋል።
የካይዘን ፍልስፍና በተለይ በአምራች ድርጅቶች ላይ የተሻለ ውጤት ማስመዘገቡንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት።
ኢንስቲትዩቱ የካይዘን ትግበራን የበለጠ ለማስፋት ከጃፓን መንግሥት በተገኘ 25 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ "የካይዘን የልህቀት ማዕከል" እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
የልህቀት ማዕከሉ ግንባታ 30 በመቶ መድረሱንና በተያዘው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
የልህቀት ማዕከሉ መገንባት ለኢትዮጵያ ተቋማት ብቻ ሳይሆን የጎረቤት አገራትም የሥልጠና ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ነው የገለጹት።