ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በንጹሐን ላይ ለፈፀመው ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦር ወንጀል መጠየቅ አለበት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) “አሸባሪው ህወሃት በንጹሐን ላይ ለፈፀመው ጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጦር ወንጀል መጠየቅ አለበት” ሲል የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያውያን አሳሰበ፡፡

ጥምረቱ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የጥምረቱ ሰብሳቢ አቶ ጋሻው ሽባባው በመግለጫው ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት የሚፈጽመውን ጥቃት ጥምረቱ በጽኑ ያወግዛል።

በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች ቡድኑ ወረራ በመፈጸም እያደረሰ ያለውን ጥቃት፣ ውድመትና ጥፋት ጥምረቱ በጽኑ እንደሚያወግዘው ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት አገር ለማፍረስ እያደረገ ያለው ተግባር ኢትዮጵያውያን በአንድነት መመከታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ቡድኑ በወገኖች ላይ ያደረሰው ጥቃት በአለም ዓቀፍ ደረጃ በጦር ወንጀል እንደሚያስጠይቀውም ተናግረዋል።

ከውስጥም ሆነ ከውጭ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና ጥምረቱ አጥብቆ እንደሚቃወም የገለጹት አቶ ጋሻው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና ጥምረቱ እንደማይቀበለው ጠቁመዋል።

“ችግሩ በአፍሪካውያን መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል” በማለት ጠቅሰው፤ “በኢትዮጵያ ጥቅም ጉዳይ ምንም ከማንም ጋር ድርድር የለንም” ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም