በዞኖቹ የወቅቱን የኢትዮጵያ እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ የፊርማ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኖቹ የወቅቱን የኢትዮጵያ እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ የፊርማ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ተጀመረ
ጂንካ/ዲላ፣ መስከረም 07/2014(ኢዜአ) በደቡብ ኦሞና ጌዴኦ ዞኖች የወቅቱን የኢትዮጵያ እውነታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ የሚያስችል የፊርማ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ተጀመረ።
በዞኖቹ በሚካሄደው መርሀ ግብር ከ40 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተነግሯል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶች ሊግ ምክትል ሀላፊ ወጣት ምትኩ ንጉሴ በመርሀ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ እንዳለው የፊርማ ማሰባሰብ አላማው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ግፍና በደል አሜሪካ እውነታውን እንድትረዳና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን እንድታቆም ለማድረግ ነው ።
አሜሪካ በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች የምታደርገው ጣልቃ ገብነት የተሳሳተና ሉዓላዊነትን የተዳፈረ ክስተት መሆኑን ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑን ገልጿል።
"የፊርማ ማሰባሰቡ የዞኑ ወጣቶችና መላው ህዝብ ከመንግስት ጎን መሆኑን ለማሳየት ያግዛል " ብሏል።
የጂንካ ከተማ ነዋሪ ወጣት ይልቃል ታምሩ በበኩሉ በነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዘመቻ ምዕራባዊያን አሸባሪው ህወሀት የሚነዛውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ተቀብለው ከማራገብ እንዲታቀቡ መልዕክት ማስተላለፉን ተናግሯል።
"ከመንግስት ጎን በመሆን በሀገራችን ህልውና ላይ የሚቃጣውን ጥቃት ለመመከት መነሳታችንን ሊያውቁት ይገባል" ብሏል።
"ነጩ ፖስታ አሜሪካንን ብቻ ሳይሆን በሀገራችን ላይ የተንሸዋረረ እይታ ያላቸው አካላትም እይታቸውን እንዲያስተካክሉና በሀገራችን ያለውን እውነታ እንዲረዱት ያግዛል" ያለው ሌላው የዘመቻው ተሳታፊ ወጣት ተሾመ መኮንን ነው።
"የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በማስተጋባት በሀገራችን ላይ ጫና ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያግዛል" ሲል ጨምሮ ገልጿል።
በደቡብ ኦሞ ዞን ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተመንግስት ዘመቻ እስከ መስከረም 15 በዞኑ በሁሉም አከባቢዎች ይካሄዳል።
በተመሳሳይ በጌዴኦ ዞን ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት የነጭ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት ዘመቻ በዲላ ከተማ ተጀምሯል።
በዘመቻው የኢትዮጵያን ሃቅ ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ከማሳወቅ በተጓዳኝ በግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ መታቀዱም ተጠቁሟል።
የዘመቻው አስተባባሪ የጌዴኦ ዞን ወጣቶች ሊግ ሃላፊ አቶ ደግነት ሃይሉ ለኢዜአ እንዳለው የኢትዮጵያን ሃቅ ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በማሳወቅ የተሳሳቱ መረጀዎችን ማጥራት የዘመቻው ዓላማ ነው።
አሸባሪው ህወሓት በንጹሀን ዜጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት ለዓለም ለማሳወቅ የዞኑ ወጣቶች ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል።
በዘመቻው በዞኑ ከ20 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን ጎን ለጎን በግጭት ለተፈናቀሉት ወገኖች "መቶ ብር ለወገኔ" በሚል ሀሳብ 1 ሚልዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ጠቁሟል።
ዘመቻውን የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደመላሽ ብሬና የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ዘማች ክፍሌ በይፋ አስጀምረዋል።