የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት 12 ሊቃነ ጳጳሳት ከአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ፍሬያማ ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት 12 ሊቃነ ጳጳሳት ከአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ፍሬያማ ውይይት አደረጉ
መስከረም 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት 12 ሊቃነ ጳጳሳት ከአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።
በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ማዕከል ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላለፉት ሁለት ቀናት በነበረው ውይይት ሊቃነ ጳጳሳቱ ውጤታማ ተልዕኮ መፈጸማቸውን አመልክቷል።
ብጹዓን አባቶቹ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ለአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አሸባሪው ሕወሐት በጀመረውና አሁንም ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ባስፋፋው የጥፋት ጦርነት በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን፣ መቁሰላቸውን እና መፈናቀላቸውን ለአሜሪካ ባለ ሥልጣናት አስረድተዋል።
የባይደን መንግሥት ትክክለኛ አቋም በመያዝ አሸባሪውን ሕወሐትን እንዳያስታምም ጠይቀዋል።
በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ያስረዱት ብጹዓን አባቶቹ፤ አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራና በከፈተው ጦርነት እያደረሰ ያለውን ቀውስና ጥፋት በዝርዝር አስገንዝበዋል።
በንጹሐን ዜጎች ላይ ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በተመለከተ ማብራሪያም ሰጥተዋል።
ቡድኑ እንደ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት ያሉ ማህበራዊ መገልገያዎችን ሆን ብሎ እያወደመ እንደሚገኝ የገለጹት አባቶቹ፤ ቤተ-ክርስቲያናትና መስኪዶችን ጨምሮ የእምነት ተቋማት የጥፋት ቡድኑ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅትን ጨምሮ የበጎ አድራጎት ተቋማት የቡድኑ የዘረፋና የውድመት ዒላማ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።
የፕሬዚዳንት ባይደን አስተዳደር የቆየውን የኢትዮጵያና የአሜሪካ ወዳጅነት ማስቀጠል የሚያስችል ሚዛኑን የጠበቀ ፖሊሲ መተግበር እንዳለበትም ብጹዓን አባቶቹ ጠይቀዋል።
አሸባሪው ቡድን የሚፈጽመውን ድርጊትና በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ የአሜሪካ መንግስት እንዲያወግዝና ጫና እንዲያደርግም አስገንዝበዋል።
የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር መስራት እንዳለበትም አባቶቹ አስረድተዋል።
ብጹዓን አባቶቹ የአሜሪካ መንግስት እያደረገ ላለው የሰብዓዊ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ውይይቱ አዎንታዊ ውጤት እንደታየበት ያመለከተው መግለጫው፤ ባለስልጣናቱ ብጹዓን አባቶቹ ያቀረቧቸውን ሐሳቦች ትኩረት ሰጥተው ማዳመጣቸውን ገልጿል።
ባለስልጣናቱ በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበው፤ ወደፊት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር በራቸው ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።