ቀጥታ፡

በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ተገቢውን አገልግሎት በማጣት መቸገራቸውን በጋምቤላ ከተማ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ተናገሩ

ጋምቤላ ነሀሴ 8/2010 በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ተገቢውን የግብር ቅሬታና የክፍያ አገልግሎት በማጣት  እየተቸገሩ መሆናቸውን በጋምቤላ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ የደረጃ " ሐ’" ግብር ከፋይ  ነጋዴዎች ተናገሩ። ነጋዴዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት የተፋጠነ የግብር ቅሬታና የክፍያ አገልግሎት ሊሰጣቸው ባለመቻሉ እየተጉላሉ ነው፡፡ ከደረጃ " ሐ" ግብር ከፋይ ነጋዴዎች መካከል አቶ ሰለሞን ጸሃይ የንግድ ፍቃድ ዘርፋቸውን ያላገናዘበ ግብር ተጥሎባቸው ቅሬታ ቢያቀርቡም ፈጣን ምላሽ በማጣት መቸገራቸውን ተናግረዋል። ሌላው ነጋዴ አቶ አብራራው አድማሴ በበኩላቸው የተጣለባቸው ግብር ከአቅማቸው  በላይ መሆኑንና ይህንን አስመልከተው ላቀረቡት ቅሬታ መፍትሄ አጥተው እየተጉላሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ቀደም ሲል ተጥሎባቸው ከነበረው ግብር በእጥፍ ተጨምሮባቸው ቅሬታ ቢያቀረቡም ነገ ዛሬ እየተባሉ ለእንግልት መዳረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ኪዳኔ አሰፋ የተባሉት ነጋዴ ናቸው ። ሌላው  ነጋዴ አቶ ወንደሙ አብዲሳ በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት  የሰው ኃይል ውስን በመሆኑ ቀልጣፋ የግብር ክፍያ አገልግሎት እያገኙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት በግብር ሰብሳቢው መስሪያ ቤት የክፍያ አገልግሎት ለማግኘት ለሳምንት ያህል እየተጉላሉ ነው፤የግብር መክፈያው ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ክፍያውንም ሆነ የቅሬታ ጥያቄያቸውን በተፋጠነ መልኩ ምላሽ ማግኘት ይፈልጋሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ገቢ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ሳይመን ኡጁሉ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ "ለነጋዴዎቹ የግብር ቅሬታና ክፍያ የተፋጠነ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል። የክፍያ መጉላላት ችግር አለ ስለተባለው ነጋዴዎች ከተሰጣቸው ጊዜ ቀድመው  ባለመምጣቸው ምክንያት በተፈጠረው መጨናነቅ  መሆኑን ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ በእረፍት ቀናት ጭምር በመስራት ለግብር ከፋዮች የተፋጠነ አገልግሎት ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በጋምቤላ ከተማ ከ2ሺህ በላይ የደረጃ '' ሐ'' ግብር ከፋይ  ነጋዴዎች እንዳሉ ተመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም