ዲላ ዩኒቨርሲቲ የአቅመ ደካሞች የቤት እደሳትና ችግኞችን መንከባከብ ጀመረ

89

ዲላ ፤ መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳትና የችግኞች እንክብካቤ ማስጀመሪያ መረሃ ግብር አካሄደ።

ዩኒቨርሲቲው በበጎ ፍቃድ አገልግሎት የራሱን አሻራ ለማሳረፍ በጌዴኦ ዞን ወናጎና ዲላ ከተሞች 13 የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት አስጀምሯል።

መረሃ ግብሩ ሲጀመር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ እንደገለጹት፤ ለቤቶቹ እድሳት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡንና በ15 ቀናት ተጠናቀው ለአገልግሎት  ይበቃሉ።

ዩኒቨርሲቲው በአረንጓዴ አሻራ ልማት ፕሮግራም ከ120 ሺህ በላይ የቀርከሃ ፣የፍራፍሬና ሌሎች  የዛፍ ዝሪያዎችን ተከላ ማካሄዱን አውስተዋል።

ችግኞች እንዲጸድቁ ውሃ የማጠጣትና ከአረም ነጻ የማድረግ ሰራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የወናጎ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ሮቤ በበኩላቸው፤  በወረዳው ከ15 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በወረዳው የጀመራቸው የሰባት ቤቶች እድሳት ለህዝቡ ያለውን አጋርነት የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፤ የአቅመ ደካሞች የቤት እድሳት በልዩ ትኩሩት እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዲላ ከተማ የቤት እድሳት የተጀመረላቸው ወይዘሮ አይናለም አላኮ በሰጡት አስተያየት፤ ቤታቸው አርጅቶ በመፍረሱ ዝናብ በስለሚያስገባ  ለችግር እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ቤታቸውን በአዲስ መልክ ለመስራት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም