አሸባሪው ቡድን ቤተሰቦቼን በግፍ ቢነጥቀኝም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኔ አልተለየም..አቶ ድረስ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ቡድን ቤተሰቦቼን በግፍ ቢነጥቀኝም የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኔ አልተለየም..አቶ ድረስ ነጋ
ደብረ ታቦር መስከረም 6/2013 ( ኢዜአ)''አሸባሪው የህወሃት ቡድን በደብረ ታቦር ከተማ በጣለው ከባድ ፈንጂ አምስት ቤተሰቦቼን በሞት ቢነጥቀኝም የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍና እገዛ መፅናኛና ጉልበት ሆኖኛል'' ሲሉ አቶ ድረስ ነጋ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት አመራሮች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎችና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደብረ ታቦር ከተማ ተገኝተው ግለሰቡን አፅናንተዋል።
አቶ ድረስ ነጋ እንደገለጹት ''እኔን የገጠመኝ ድንገተኛና ልብ ሰባሪ ሃዘን በህይወት ቆሜ እያለሁ ለአፍታም ቢሆን ልረሳው የማልችል ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ በደል ነው'' ብለዋል።
ነሃሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ሃገር አማን ነው ብልው ወደ ቤተክርስቲያን መሄዳቸውን አስታውሰው፤ አሸባሪው ቡድን የደብረ ታቦር ከተማን ለማውደም በነበረው የፀና ፍላጎት በጣላው ከባድ ፈንጅ ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ማለቃቸውን ገልፀዋል።
በአደጋውም የ44 ዓመታት የትዳር አጋራቸውን ጨምሮ ባለፈው ሐምሌ ወር 2013 ላይ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀ ወንድ ልጃቸው፣ሁለት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሴቶችና አንድ ህጻን ልጃቸው በአሸባሪው ቡድን ጥቃት ህይወታቸው አልፏል።
''ቤተሰቦቼ በድንገት በሞት ሲለዩኝ የደረሰብኝ ሃዘን እንደሰው ልቋቋመው ያልቻልኩት የሚከብድ እጅግ አስጨናቂ ነው'' ያሉት አቶ ድረስ "ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኔ ሆኖ እያጽናናኝ ነው" ብለዋል።
ድርጊቱ ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ህዝቡ ከጎናቸው እንዳልተለያቸው ጠቅሰው፤ ሃዘናቸውን አምቀው በህዝቡ ድጋፍና እገዛ እየተፅናኑ ጉልበት እያገኙ እንደሆነ አመልክተዋል።
በጥቃቱ የወደመው መኖሪያ ቤታቸው በደብረታቦር ከተማ ህዝብ እንደተሰራላቸው የገለፁት አቶ ድረስ "ህዝቡ ከቤታቸው እንዳልጠፋ ነው" የገለጹት።
''በኢትዮጵያ ህዝብ ኮርቻለው'' የሚሉት አቶ ድረስ ማን እንደሆነ የማያውቁት ሁሉ እየደወለ የማጽናኛ ቃልና የገንዘብ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የደረሰባቸው ሃዘን ከባድ ቢሆንም ''አይዞህ ከጎንህ ነን'' የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ብርታት እንደሆናቸው ገልፀዋል።
በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በየቀኑ በመደወል እያጽናናቸውና በገንዘብ እያገዛቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ የማይረሳ ጠባሳ እንዳሳረፈባቸው ገልፀው "ይህንን አሸባሪና አረመኔ ቡድን እስከመጨረሻው ደምስሶ ማጥፋት ህዝብንም ሃገርንም ማዳን ነው" ብለዋል።
''ያደረሱት ግፍና በደል በእኔ ይብቃ'' ያሉት አቶ ድረስ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሀገር መከላከያ ስራዊት አመራሮችና የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች በቤታቸው ተገኝተው በማጽናናታቸው አመስግነዋል።