ቀጥታ፡

በአሸባሪው ወረራ የተጎዱ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም አለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

ባህርዳር፤ መስከረም 6/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው ወረራ የተጎዱ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም አለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ጥሪ አቀረቡ።

 ርዕሰ መስተዳድሩ በተባበሩት  መንግስታት   የምግብና እርሻ ድርጅት ሉዑካን  ቡድን ጋር ዛሬ በባህርዳር ከተማ በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት፤ አሸባሪው ህወሃት በአምስት ዞኖች  ላይ ወረራ በመፈጸም በንጹሃን ላይ የሞት፣ ማፈናቀል ፣ የሃብት  ዘረፋና  ውድመት  አስከትሏል።

አሸባሪው ቡድን በገባባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሩን ምርት ቤት ለቤት እየገባ በመዝረፉ አሁን ላይ ከ4 ሚሊየን በላይ ህዝብ በችግር ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ህዝብ ደግሞ ተፈናቅሎ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በማውደማቸው ህብረተሰቡ ለችግር መጋለጡን አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ የዘራውን  ሰብልም  አሸባሪው ቡድን  እያወደመበት  ስለሚገኝና  መንከባከብ  ባለመቻሉ ከስራ ውጭ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ይህ ሁሉ በደልና ግፍ በህዝብ ላይ እየተፈጸመ አለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች በችግሩ ልክ  ትኩረት አለመስጠታቸው  አሳዛኝ መሆኑን አንስተዋል።

ወረራ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የሚገኘው አርሶ አደር ቤተሰቡ ያለበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ  በማስገባት አለም አቀፍ ረጂ ድርጅቶች ከእለት ምግብ  ማቅረብ  ጀምሮ በዘላቂነት  የሚቋቋሙበትን  ሁኔታ በመፍጠር  ድጋፍ  እንዲያደርጉ  ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ  ተወካይ ሚስ  ፋጡማ ሰይድ በበኩላቸው፤ በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል   ህዝቡ ችግር  ውስጥ መግባቱን መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የደህንነት ስጋት ያደረባቸው አርሶ አደሮች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀላቸው በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ዋና ተግባሩ በግብርናው ዘርፍ ሰብልና ዓሳ ልማት እንዲሁም በግብርናው የሚሰማራውን የግሉ ዘርፍ ማጠናከርና የምርት ብክነትን መቀነስ መሆኑን አስረድተዋል።

ሆኖም አሁን ላይ  ከተከሰተው  የሰላም መታጣትና  አለመረጋጋት  አርሶ አደሩን በምን  ያህል ደረጃ እንደጎዳው በመገምገም ካለበት ችግር እንዴት ልናወጣው እንደምንችል እየተወያየን ነው ያሉት።

የደረሰውን ጉዳት መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከበላይ  ሃላፊዎቻቸው ጋር በመምከር  አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የእምቦጭ አረም በጣና ሃይቅ ላይ እየፈጠረ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት  በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ድርጅታቸው እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በተለይም በምስራቅ አማራ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የአንበጣ መንጋ በክልሉ ምርታማነት ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ በሚቻልበት ላይ ለመስራት  መግባባት  ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

በመኸሩ ወቅት የለማው ሰብል አሰባሰብ፣  መውቃት፣  ማጓጓዝና ማከማቸት  ጋር ተያይዞ  የሚደርስ  የምርት ብክነትን ለመቀነስ እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊና በተባበሩት  መንግስታት   የምግብና እርሻ ድርጅት የፕሮጀክት ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም