ቀጥታ፡

ወቅቱ በመተባበር ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና የምናሻግርበት ነው

ደሴ፤ መስከረም 6/2014 (ኢዜአ) ወቅቱ የቀደመ አንድነታችንና ትብብራችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ከገጠማት ወቅታዊ ፈተና የምናሻግርበት ነው ሲል አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ አስታወቀ።

አትሌቱ በአሸባሪው ህወሃት ተፈናቅለው በኮምቦልቻ የተጠለሉ ወገኖችን በመጎብኘት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው የምግብ ድጋፍ አድርጓል።

አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በወቅቱ እንደገለፀው ቡድኑ ጦርነቱን የግብርና ስራ በሚከናወነበት የክረምት ወቅት መክፈቱ ችግሩን የከፋ አድርጎታል።

"አርሶ አደሩ የዓመት ቀለቡን በሚያመርትበት የመኸር ወቅት ከመሆኑ ባለፈ ያለው ንብረት መዘረፉና መውደሙ በእጅጉ ያሳዝናል" ብሏል።

"ቡድኑ ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ በመሆኑ አንድነታችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ከገጠማት ውስብስብ ችግር የምንታደግበት ወሳኝ ሰዓት ነው" ሲል ተናግሯል።

በተለያየ ጊዜ የጥፋት ቡድኖች በሚፈጥሩት ግርግር በርካታ ንብረት መውደሙን ጠቅሶ እሱም የጉዳቱ ሰላባ መሆኑን ጠቅሷል።

በተለይም  በዋግኽምራ የሰራው ትምህርት ቤት በወራሪው ሀይል መፍረሱ እጅግ ያሳዘነው መሆኑን ገልጿል፡፡

"ሁሉንም ፈተና በጋራ በድል እንደምናልፈው አልጠራጠርም" ያለው አትሌቱ ፤ "የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለማስጠበቅ እስከ ህይወት መስዋእት ለመክፈል ሁላችንም ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል" ብሏል።

አትሌቱ ለተፈናቃዮች 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው 500 ኩንታል ዱቄትና 2 ሺህ 500 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ አበርክቷል ።

በአፋር ለተፈናቀሉም ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰይድ በበኩላቸው፤ አሸባሪውን ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ የሚደነቅና መቀጠል ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ ደሴን፣ ሐይቅን፣ ኮምቦልቻንና ሌሎችንም ከተሞች ለመዝረፍና ለማውደም ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ መክሸፉን ተናግረዋል።

አሁንም በተለያየ አቅጣጫ ሰርጎ ለመግባት ሙከራ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ "በቅንጅት እየተመታና እየተደመሰሰ ይገኛል" ብለዋል።

"የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን አንድነት አጠናክሮ ቡድኑን ዳግም ስጋት በማይሆን መልኩ መቅበር ይጠበቅበታል" ሲሉም አመልክተዋል።

በድጋፉና ጉብኝቱ የዞንና የከተማ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም