በቱር ርዋንዳ ኢትዮጵያውያን ወክለው የተወዳደሩ ብስክሌተኞች ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቱር ርዋንዳ ኢትዮጵያውያን ወክለው የተወዳደሩ ብስክሌተኞች ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል
አዲስ አበባ ነሀሴ 8/2010 በቱር ርዋንዳ ኢትዮጵያውያን ወክለው የተወዳደሩ ብስክሌተኞች ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል። የብስክሌት ተወዳዳሪዎቹ ዛሬ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የስራ ሃላፊዎች አቀባባል አድርገውላቸዋል። ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በተካሄደው ዓመታዊው ቱር ርዋንዳ የብስክሌት ውድድር 16 አገሮች ተሳትፈው ኢትዮጵያ አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠቃላለች። ርዋንዳ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ሆናለች። ዘርአይ ገብረጻዲቅ፣ ገብረመድህን ግርማይ፣ በረከት ደሳለኝ፣ ሙሉ ክንፈና ተመስገን መብራቱ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ ብስክሌተኞች ናቸው። የቱር ርዋንዳ ውድድር በስምንት ዙር ተከፍሎ በአጠቃላይ 953 ኪሎ ሜትር የሸፈነ ነው። የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግዛቸው መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዘንድሮው የቱር ርዋንዳ ውድድር ያስመዘገበችው ውጤት ሰባተኛ ደረጃ ይዛ ካጠናቀቀችበት ያለፈው ዓመት የተሻለ ነው። የብስክሌት ተወዳዳሪዎቹ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ተመጣጣኝ ፉክክር ማሳየታቸው በአህጉራዊ የብስክሌት ውድድሮች ላይ ተሳትፎአቸውን በማሳደግ የተሻለ ውጤት ማምጣቱ የሚጠቁም እንደሆነ ገልጸዋል። በዳገት የብስክሌት ውድድር ሙሉ ክንፈ አንደኛ የወጣ ሲሆን ተመስገን መብራቱ በሜዳ ላይ የብስክሌት ውድድር ሶስተኛ መውጣቱን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በየካቲት ወር 2010 ዓ.ም በርዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በተደረገው 16ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ውድድር ሶስት የወርቅ፣ ሰባት የብርና ሶስት የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 13 ሜዳሊያ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋን አስታውሰዋል። በተጨማሪም በጥር ወር 2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ በጋቦን በተካሄደው ቱር አሚሳቦንጎ የብስክሌት ውድድር ከአፍሪካ አገሮች ሁለተኛ መውጣቷንም አንስተዋል። በአጠቃላይ በዘንድሮው ዓመት በአህጉራዊ የብስክሌት ውድድሮች ኢትዮጵያ መልካም የሚባል ውጤት ማስመዝገቧንና ስፖርቱ ላይ ይበልጥ ከተሰራ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመልክተዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብስክሌት ተወዳዳሪው ጽጋቡ ገብረማርያም በዓለምና አህጉር አቀፍ የብስክሌት ውድድሮች ያስመዘገበው ውጤት በስፖርቱ ዘርፍ መነቃቃት ፈጥሯል። ጽጋቡ ኢትዮጵያ በብስክሌት ስፖርት ከኦሎምፒክ ተሳትፎ ከራቀች ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ በ31ኛው የሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር አገሩን ወክሎ መሳተፉና በዚያም ላይ ያሳየው ብቃት ተዳክሞ ለቆየው የብስክሌት ስፖርት ዳግም መነቃቃት መፍጠሩ ይታወቃል።