ቀጥታ፡

ወጣቱ አሸባሪ ቡድኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ስቃይ ለአለም ማሳወቅ አለበት- ዶክተር ድረስ ሳህሉ

ባህርዳር/ደሴ፤መስከረም 06/2014 (ኢዜአ) ወጣቱ አሸባሪ ቡድኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ስቃይ ለአለም ማሳወቅ አለበት ሲሉ -የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ተናገሩ።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና በደቡብ ወሎ ዞን ''ነጩ ፖስታ ለነጩ ቤተ መንግስት'' ዘመቻ  ተጀምሯል።

ዶክተር ድረስ ሳህሉ  በባህርዳር ስነ-ስርዓቱ  ላይ  እንዳሉት፤  አሸባሪው  ህወሃት  የአማራና የአፋርን ክልል በመውረር ዜጎች ላይ ግፍና በደል እየፈፀመ ነው።

''የነጩ ፖስታ ጎርፍ ለነጩ ቤተ መንግስት''በሚል በከተማ  አስተዳደሩ  የተጀመረው  ፊርማ የማሰባሰቡ ተግባር የህልውና ዘመቻው አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

 መርሃ ግብሩ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት በአሸባሪው  የህወሃት  ቡድን  በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል እንዲሁም ደባና ሴራ  ቆምብለው እንዲያስቡ ለማድረግ ታስቦ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።  

ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣት የዚህ ታሪክ ተጋሪ በመሆንም አሸባሪ ቡድኑ በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን መከራና ስቃይ   ለሌላ አለም የማሳወቅ ኃላፊነት አለበት ብለዋል።

የክልሉን ባለሃብቶች በመወከል በመድረኩ ላይ የተገኙት አቶ በላይነህ ክንዴ ''አባቶቻችን ኃይላቸውን አስተባብረው ጠላትን አሸንፈው ያስረከቡንን ሀገር አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሊበትናት አይገባም'' ብለዋል'

አሸባሪው ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ያበላቸውንና ያጠጣቸውን ህዝብ ረሽኗል፣ አዋርዷል በመሆኑም ጠላትን በመፋለም ህዝቡን ከተጋረጠበት  የህልውና  አደጋ  ችግር ልናድነው ይገባል ነው ያሉት።

ይህንን ሽፍታና ወራሪ ኃይል የአሁኑ ወጣት እንደቀደሙ አባቶቹ በመፋለም ሀገሩን ከብተና፣ በዜጎች ላይ የሚፈፀምን ግፍና በደል በመታገል ህዝቡን ሊታደግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

''እኛ ባለሃብቶችም ኢትዮጵያን ከአሽባሪው ቡድንና ከውጭ ጠላት ለመታደግ ለሀገሩ ዘብ ለሚቆመው ወጣት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ  ነን'' ብለዋል።

የባህር ዳር  ከተማ አስተዳደር  ወጣቶች  ፌደሬሽን  ፕሬዚደንት ወጣት  ዘላለም ታከለ ፤ አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት  አሸባሪውን በመደገፍ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ተናግሯል።

ይህንኑ ያልተገባ ጫና  ለመቃወም በሚካሄደው የፊርማ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ከ20 ሺህ በላይ ፈቃደኞች ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጿል።

በተመሳሳይ በደቡብ ወሎ ዞን 50 ሺህ በላይ ወጣቶች የሚሳተፉበት ''ነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት'' መርሃ ግብር ዛሬ ተጀምሯል።

የዞኑ  የወጣቶች ሊግ ሰብሳቢ ወጣት አብዱ መሀመድ  በወቅቱ  እንዳለው   የፊርማው  ዓላማ የአሸባሪው የህውሃት ቡድን የሴራ ፖለቲካና ድርጊት ለዓለም ህዝብ ለማሳወቅ ነው።

 መርሃ ግብሩ  አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት  እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የሚደረገው ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ አካል መሆኑን ተናግሯል።

ወጣት መስፍን የሱፍ በበኩሉ'' የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የማንከፍለው መስዋትነት የለም'' ብሏል።

ሀገራቱ እውነቱን ተገንዝበው አሸባሪውን ቡድን ከመደገፍ ተቆጥበው ኢትዮጵያን እንዲያግዙ የተጀመረው ግፊት በተደራጀ አግባብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም