በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
መስከረም 6፣2014 (ኢዜአ) በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ዜጎች በተጨማሪ በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል አስታወቁ።
የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃያት ካሚል በኢትዮጵያ ከአሜሪካን አምባሳደር ጊታ ፓሲ እና የአሜሪካን ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያ ሚሽን ዳይሬክተር ሾን ጆንስ ጋር የሰብዓዊ ድጋፍን ማጠናከርና ማስፋፋት በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ውይይቱ አሸባሪው የህውሃት ቡድን ባደረሰው ጥቃት በአማራ እና አፋር ክልሎች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የዕለት ደራሽ እርዳታ በአፋጣኝ ለማዳረስ እና የመልሶ ማቋቋም ፈጣን ምለሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ስልቶችን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ሚኒስትሯ በመንግስት በኩል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ዜጎች በተጨማሪ በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከቀዬአቸው ርቀው የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ለዚህም የሰብዓዊ አጋሮች ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አመልክተዋል።
አምባሳደር ፓሲ በበኩላቸው እየተደረገ ያለውን ጥረት የሚከታተሉ መሆኑን ገልጸው፤ የአሜሪካን መንግስት እና ህዝብ ለረጅም ዘመናት የቆየውን ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ የሰበዓዊ ድጋፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ሚስተር ሾን ጆንስ በበኩላቸው የአሜሪካን ተራድኦ ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች በተለያዩ አካባቢዎች እየተደረገ ያለውን ሰብዓዊ እርዳታ ርብርብን እያገዘ መሆኑንና የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎች ላይ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ድጋፉ በስፋት ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከሰላም ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።