ቀጥታ፡

ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ሀገሩን በታማኝነት ካገለገለ ወታደርም ጀግናም ነው

ሀዋሳ መስከረም 5/ 2014 (ኢዜአ) ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ሀገሩን በቅንነትና በታማኝነት ካገለገለ ወታደርም ጀግናም ነው ።

ህወሃት በሀገር ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ከሶስት ዓመት በፊት በፈቃዳቸው ወደሚወዱትና ለቀውትወደነበረው የውትድርና ሙያ የተመለሱት መቶ አለቃ አይዳ አላሮ የብላቴ የልዩ ዘመቻዎች ሀይል ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ ናቸው።

"ማንም ከሀገር በላይ አይደለም" ያሉት መቶ አለቃ አይዳ ህወሃት በሀገር ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ ለመመከት ሲሉ  ወደ አሰልጣኝነታቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

"የሀገሬ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ከምንም በላይ ያሳስበኛል" ያሉት መቶ አለቃዋ በአሁን ሰዓት ወታደር ለመሆን የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጨምሮ ሳይ ደስታዬ ወደር የሌለው ሆኗል" ብለዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት ወታደሮችን ለመመልመል ብዙ ቅስቀሳና መከራ እናይ ነበር፤ አሁን ውትድርና እንደ ሙያ የሚታይበት ክብር ያገኘ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ወታደር ለመሆን ሰራዊቱን የሚቀላቀል ዜጋ መብዛቱ ኢትዮጵያዊነት ዝም ተብሎ የሚተው እንዳልሆነና ህዝቡ በሀገር ጉዳይ እንደማይደራደር ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል ።

"ኢትዮጵያዊያን ምንጊዜም ጀግኖች ናቸው" ያሉት መቶ አለቃ አይዳ "ወታደር ስትሆን በአውደ ውጊያም ሆነ በሰላም ወረዳ እንዲሁም ሲቪል ስትሆን ደሞ በተሰማራህበት ሙያ ጀግንነትን ማሳየት ግድ ይላል" ብለዋል።

ለሀገር ወታደር ለመሆን የግድ ዩኒፎርም መልበስና ክላሽ መታጠቅ እንደማይጠበቅ የተናገሩት አሰልጣኟ ሁሉም በተሰማራበት የሙያ መስክ ለሀገሩ በተገቢው መንገድ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገልና ስኬታማ መሆን እስከቻለ ድረስ ወታደር ነው፤ የሚል እሳቤ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

መቶ አለቃ አይዳ ቀደም ባሉት አመታት በብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት 34 ጊዜ ከአየር የዘለሉ ብቸኛዋ ሴት አየር ወለድ እንደሆኑና ወደፊትም እድሉን ካገኙ ያለማቋረጥ መዝለል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በብላቴ ልዩ ዘመቻዎች ሀይል ማሰልጠኛ ማዕከል በልዩ ሀይልነት ተመልምለው በስልጠና ላይ ከሚገኙ መካከል ምልምል ወታደር አስረሳኸኝ መልካሙ "ኢትዮጵያ ስትነካ አልወድም" ብለዋል።

"ኢትዮጵያ በርካታ ጀግና ወታደሮች አሏት፤ ወደ ውትድርና ስገባ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አልጠበኩም ነበር፤ ሆኖም ግን ከጠበኩት በላይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፤ እንደእኔ ሁሉም ለሀገሩ በየሙያው ወታደር መሆን አለበት" ሲሉ ገልጸዋል።

"ውትድርና ማለት ፍቅር ነው፣ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በአንድነትና በፍቅር የሚኖሩበት ሙያ ነው" ያሉት ደግሞ የልዩ ሀይል ሰልጣኝ ወታደር ነብዩ እቅዱ ናቸው።

"በሲቪል ህይወቴ እንዲህ አይነት ፍቅር አላገኘሁም፤ በዚህ ቆይታዬ ያገኘሁት ፍቅር ለሀገሬ ህይወቴን በመስጠት ባንዲራዋ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ እሰራለሁ" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም