ሰብዓዊ ድጋፍ ለማንኛውም ተጎጂ ያለ ቅድመ ሁኔታ መሰጠት ያለበት አገልግሎት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሰብዓዊ ድጋፍ ለማንኛውም ተጎጂ ያለ ቅድመ ሁኔታ መሰጠት ያለበት አገልግሎት ነው
መስከረም 4 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ሰብዓዊ ድጋፍ ለማንኛውም ተጎጂ ያለ ቅድመ ሁኔታ መሰጠት ያለበት አገልግሎት ነው" ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡
አሸባሪው ህውሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ምክንያት ቁጥራቸው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለጉዳት መዳረጋቸውም ተገልጿል።
ዛሬ የሰላም ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የሰብዓዊ እርዳታን በማስተባበር እና በማዳረስ ላይ የተሰማሩ የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች አለም ዓቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ህውሃት በንፁሃን ላይ የሚፈጽመውን ጥፋት ለማስፋፋት ባለው ፍላጎትና ባደረሰው ጥቃት ቀድሞ በመጠለያዎች ከሚገኙ ወገኖቻችን በተጨማሪ በቅርቡ ከ550,000 በላይ ዜጎቻችን ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውና አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡
የጥፋት ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች እርዳታ እንዳይደርስ የማደናቀፉን ሂደት መቀጠሉ ከተራብን ጩሀት ወደ ረሀብን በመፍጠር የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለመሳብ የሞት ሽረት ትግል እያካሄደ መሆኑን ያሳያል ተብሏል።
ሚኒስትሯ አክለውም በአማራ እና አፋር ክልሎች የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች እገዛ እጅጉን አናሳ በመሆኑ ድርጅቶቹ ድጋፋቸውን በማስፋት ሁለቱን ክልሎች የማገዝ የሞራልም የተቋቋሙበት የሰብዓዊ ስራ መመሪያም ግዴታ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
እንደ ትግራይ ክልል ሁሉ በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚገኙ ወገኖች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ መሰረተ ልማት ወድሟል።
ስለሆነም “አለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ያደረጉትን ጊዜ፣ ቦታ እና የጦር ቀጠና ተግዳሮቶች ያልገደቡትን ርብርብ ያህል ትኩረት ሰጥተው በአማራ እና አፋር ክልሎች ድጋፍ ማድረግ ይገባል” ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ሙፍሪሃት ህወሃት እርዳታ ማዳረስን ሆን ብሎ በማደናቀፍና መንገድ በመዝጋት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ መሆኑንም በግልጽ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባቸው አስታውቀዋል።
ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ጭነው የገቡ የጭነት መኪኖች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ያልተመለሱ በመሆኑ ኃላፊነት ወስደው ያሰማሯቸው ሰብዓዊ ድርጅቶች በአስቸኳይ ወደማዕከል መመለሳቸውን አረጋግጠው ሪፖርት እንዲያቀርቡ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት የተለየ ትኩረት በሚፈልጉ የሰሜን ወሎ፣ ዋግህምራ እና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት በባህር ዳር፣ ደሴ፣ ሰሜን ጎንደር እንዲሁም በአፋር ክልል ሰመራ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከላት ተከፍተው ባለሙያዎች ተመድበው እርዳታ የማዳረስ ስራውን በተሻለ ቅንጅት ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና በብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጥረት ቀደም ሲል ያልነበሩ ውስን የሰብዓዊ ድርጅቶች ወደ ክልሉ ገብተው ስርጭት የጀመሩ ቢሆንም በቂ ያለመሆኑ ተገምግሟል። በተወሰኑ የሰሜን ወሎ ወረዳዎችም እርዳታ ማድረስ ጀምረዋል። በደቡብ ወሎ ከሰሜን ወሎ ለተፈናቀሉ እንዲሁም በዋግህምራ ዞን ቀደም ሲል ነጻ በሆኑ አካባቢዎች ላይ በተወሰነ ደረጃ ስርጭት ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ከዋግ ህምራ ዞን ተፈናቅለው የተለያዩ ጣቢያዎች ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችንም የዕለት ደራሽ እርዳታ እየተሰራጨ መሆኑ ተገምግሟል።
የአጋር ድርጅቶቹ ተወካዮች የተነሱት ስጋቶች ትክክለኛ በመሆናቸው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ወጥ የሆነና የተቀናጀ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ በአስቸኳይ የጋራ እቅድ አውጥተው በክልሎቹ ከሚንቀሳቀሱ የፌደራል እና የክልል ማዕከላት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ሰብዓዊ ተኩስ አቁም ከወሰነበት ጊዜ ወዲህ አሸባሪው ቡድን ህውሃት በአማራ እና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ ምክንያት ቁጥራቸው 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚገመት ዜጎች ለጉዳት ተዳርገዋል።
በመሆኑም ሁሉም የሰብዓዊ አካላት ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው ከመንግስት ጎን በመቆም ጉዳት የደረሰባቸውንና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመታደግ ከመቼውም በበለጠ ተቀናጅቶ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።