ቀጥታ፡

በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያንሰራራ ተቀናጅቶ መስራት ይገባል

ድሬዳዋ ፤ መስከረም 04/2014(ኢዜአ) በድሬዳዋ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ዳግም አንሰራርቶ ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ።

"ቱሪዝም ለሁለንተናዊ ዕድገት" መሪ ሃሳብ የአለም የቱሪዝም ቀን ዛሬ በድሬዳዋ በፅዳት፣ በችግኝ ተከላና በብስክሌት ውድድር  ተከብሯል፡፡

በዚህ ወቅት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ፤ የኮሮና  ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና ከፈጠረባቸው ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጫናውን በመቋቋም ዘርፉን ለማሳደግና ምጣኔ ሃብታዊ ጠቀሜታውን ትርጉም ባለው መንገድ ለመለወጥ በዘርፉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮልን በመጠበቅ ዘርፉን ለማሳደግና በየደረጃው የሚገኘውን ህብረተሰብ ንቃተ ህሊና በማሳደግ የሚገኘውን ጥቅም ትርጉም ባለው መንገድ መለወጥ ይገባልም ብለዋል፡፡

"የድሬዳዋ አስተዳደር የቱሪዝም መስቦችንና የቱሪስት መዳረሻዎችን ማራኪና ሣቢ እንዲሆኑ ይሰራል "ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ በበኩላቸው፤ የኮሮና ወረርሸኝ የቱሪስት መዳረሻዎችና የቱሪስት መዝናኛዎችን በመዝጋትና የዘርፉን ጥቅም በማሳጣት ተጽዕኖ ፈጥሮ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

አሁን ግን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ዘርፉን ወደነበረበት ለመመለስ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ቱሪዝም ለሁለንተናዊ ዕድገት" መሪ ሀሳብ ዛሬ በድሬዳዋ መከበር የጀመረው የቱሪዝም ቀን ዘርፉን ለማነቃቃት እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

ድሬዳዋ ከሺህ ዓመታት በፊት የመካከለኛ ሰው ይኖርባቸው የነበሩ ዋሻዎችና የዋሻ ስዕሎች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ከመቶ አስራ ስምንት ዓመታት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው ጥንታዊ የባቡር ትራንስፖርት ድርጅት ልዩና ቀልብ የሚስቡ ታሪካዊ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ የገለጹት አቶ ሙራድ፤ የድሬዳዋ ቤተመንግስትም ለቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መታደሱን ተናግረዋል፡፡

"እነዚህን ሃብቶች ለማስተዋወቅ በዓሉ ልዩ አጋጣሚ ይፈጥራል" ብለዋል፡፡

በኮሮና ወረርሽኝ የተጎዳውን የቱሪዝም ዘርፍ ዳግም ወደነበረበት ለመመለስ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተቀናጅቶ መስራት  እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ክብሮም ታደለ ናቸው፡፡

የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮል ጠንቅቆ በማክበር የዘርፉን ጥቅሞች ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

ዘንድሮ በሃዋሳ ከመስከረም 8 ጀምሮ መከበር የሚጀምረው የአለም የቱሪዝም ቀን የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በድሬዳዋ ተገኝቶ ባህሉን ማክበር ፣ተቀናጅቶ የመስራትን መሠረታዊነት ለማጽናትና ህዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር መሆኑን ነው አቶ ክብሮም የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም