የሰበታ ከተማ ገበያ የማረጋጋት እንቅስቃሴ ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ ሊሆናቸው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰበታ ከተማ ገበያ የማረጋጋት እንቅስቃሴ ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ ሊሆናቸው ይገባል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ ገበያ የማረጋጋት እንቅስቃሴ ለሌሎች ከተሞችም ተሞክሮ ሊሆን እንደሚገባ ተነገረ።
የከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት ተደብቀው የነበሩ ምርቶች ወደ ገበያ እየወጡ መሆኑንም ገልጿል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሰበታ ከተማ ገበያ ለማረጋጋት የተወሰዱ እርምጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን አስጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ገበያውን ለማረጋጋት ሲባል በመጋዘኖች የነበሩ ሩዝ፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ዱቄትና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች ተጎብኝተዋል።
የሰበታ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታዬ ዋኬኔ እንደተናገሩት፤ የኑሮ ውድነት ችግሮችን ለመፍታት በከተማው ከንቲባ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ተገብቷል።
ከ12 ሺህ በላይ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት መካሄዱንና የከተማው ነዋሪም ህገ ወጥነትን ሲያይ ለመብቱ መታገል የሚያስችለው ግንዛቤ እንዲያገኝ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መታየቱንና የዋጋ መረጋጋት መፈጠሩን አክለዋል።
ፈሳሽ ዘይት 680 ብር ድረስ ይሸጥ እንደነበር አስታወሰው አሁን ከ530 እስከ 510 ድረስ እየተሸጠ ነው ብለዋል።
ከግንባታ እቃዎች ጋር በተያያዘ በአንድ እቃ ከ50 እስከ 120 ብር ድረስ ቅናሽ ማሳየቱን፤ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረሰ መግባባት በመጋዘኖች ተከማችተው የነበሩ ምርቶች ገበያውን ለማረጋጋት ገበያ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
በተለይም ለዳቦ ምርት የሚሆነውን ዱቄት አቅራቢዎችና አምራቾችን በማስተሳሰር ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አቶ ታዬ አብራርተዋል።
በዚህም ትንሹን ዳቦ 65 ግራም አድርሰው የነበሩ ዳቦ ሻጮች ወደ 100 ግራም ማስተካከለቸውን ጠቅሰዋል።
ዋጋ በማናር፣ ያለ ደረሰኝ በመሸጥና ወደ ህጋዊ መስመር ባለመግባት ሰባት የንግድ ተቋማት ላይ ክስ ተመስርቶ የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የዘይትና ስኳር አስመጪና ጅምላ አከፋፋይ ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት አወል ዚያድ መንግሥት ከታክስ ማሻሻያ ጋር ያሳለፈው ውሳኔ ምርትን ለሸማቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ጉልህ ፋይዳ አለው ብሏል።
አገርና መንግሥት እየተቸገረ የእኛ ገቢ ቢጨምር ምንም ትርጉም የለውም ሲልም ተናግሯል።
የሰበታ ከተማ ከንቲባ ብርሃኑ በቀለ በበኩላቸው በከተማው ገበያውን በማረጋጋት ረገድ ውጤት ቢገኝም በቂ አይደለም፤ የበለጠ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አበባ ታመነ በአገሪቷ የምርት ችግር እንደሌለና የሚስተዋለው በአሻጥር እጥረት የመፍጠር እንቅስቃሴ እንደሆነ ተናግረዋል።
ምርቶች በአግባቡ ሸማቹ ዘንድ እንዲደርሱ ቅንጅታዊ አሰራሮች ሊጎለብቱ እንደሚገባ ነው የገለጹት።
ዜጎች ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ጥቆማ መስጠት መጀመራቸው የሚበረታታ መሆኑንና ችግሩ ሙሉ በሙሉ ባለመፈታቱም ይኸው መቀጠል እንዳለበት ነው ዳይሬክተሯ ያሳሰቡት።