በስምንት ኮንቴይነር የታሸገ የኤሌክትሪክ እቃና አልባሳት በህገ-ወጥ መንገድ ሲገባ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በስምንት ኮንቴይነር የታሸገ የኤሌክትሪክ እቃና አልባሳት በህገ-ወጥ መንገድ ሲገባ ተያዘ

አዳማ ነሀሴ 8/2010 በጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ጥሬ እቃ ስም በስምንት ኮንቴነር የታሸገ ያለቀለት የኤሌክትሪክ እቃና አልባሳት ወደ ሃገር ውስጥ ሊገባ ሲል መያዙን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ። በባለስልጣኑ የሞጆ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የጉምሩክ ስነ-ስርዓት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ግርማ በንቲ ዛሬ እንደገለጹት እቃው የተያዘው ተመሳስሎ ሊያልፍ ሲል በሞጆ ደረቅ ወደብ ላይ ነው። በአምስቱ ኮንቴነሮች የተያዘው ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የሚውል ብትን ጨርቅ እንደሆነ ተመስክሮለት በጁቡቲ ወደብ የገባ ቢሆንም በተደረገ ፍተሻ ከምርት ጋር ተመሳስሎ የታሸገ 410 ቦንዳ ያለቀለት አዳዲስ አልባሳት ሆኖ ተገኝቷል።
ከተያዙት አልባሳት መካከልም ያለቀለትና ለገበያ ሊበተን የሚችል በርካታ ዘመናዊ ጃኬትና ሱሪ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል። በሶስቱ ኮንቴነሮች የተያዘው ደግሞ ለፋብሪካ በጥሬ እቃነት የሚውል የክር ማግ መሆኑን ተመስክሮለት ወደ ሀገር ውሰጥ እንዳይገባ የተከለከለ የኤሌክትሮኒክስ እቃ መሆኑን ጠቁመዋል። የኤሌክትሮኒከስ እቃው በአንድ ሺህ 500 ካርቶን የታሽገ በለ 200 ዋት 75 ሺህ አምፖል መሆኑንም አመልክተዋል። “ይህ ምርት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አባካኝ መሆኑ በሚመለከተው የመንግስት አካል የተረጋገጠ በመሆኑ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለ ነው” ብለዋል። በኮንቴነሮቹ ላይ የነበረው አጫጫን ሲታይ ህጋዊ እቃዎችን ከፊት በመደርደር ህገ ወጦቹን ከኋላ በመደበቅ የጉምሩክ ኦፊሰሮች እንዳይደርሱበት ከጥሬ ዕቃው ጋር ተመሳሳይ በሆነ መጠን ለማስቀመጥ መሞከሩን ተናግረዋል። በአጠቃላይ ከጉምሩክ እይታ ውጪ በማድረግ ሸሽጎ ለማስገባት የተሞከረው እቃ በስምንቱ ኮንቴነር ውስጥ ከነበረው ህጋዊ እቃ ከ50 በመቶ ይበልጣል ብለዋል። የንብረቱ የዋጋ ግምት እየተሰላ መሆኑን ገልጸው ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ እንዲጣራ ለጉምሩክ ህግ ማስከበርና ምርመራ ክፍል መተላለፉን አስታውቀዋል።
