ቀጥታ፡

የአሸባሪ ቡድኑን አገር የማፍረስ እኩይ ተግባር ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እናስረዳለን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 04/2014 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የወጠነውን ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ተግባር ተረድቶ እንዲያወግዘው ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ወጣቶች ገለጹ።

አስተያየታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ ወጣቶች "የነጩ ፖስታ ጎርፍ ወደ ነጩ ቤተ መንግስት" የተሰኘውን ዘመቻ እየተቀላቀሉ ናቸው።

የኢትዮጵያን እውነታና የአሸባሪውን ህወሓት የጥፋት ሴራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳየት በዘመቻው መሳተፋቸውንም ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡

ወጣቶቹ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአሸባሪውን ቡድን 'እኔ የማልመራት አገር ትፍረስ' የሚል አኩይ ዓላማ ሊረዳው ይገባልም ብለዋል፡፡

ለዚህም ለአሜሪካው ነጩ ቤተ-መንግስት የሚደርሰውን ደብዳቤ በመፈረም በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ ዘመቻም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አሸባሪው ቡድን ላይ ተጽእኖ እንዲያሳድር በማሰብና ከኢትዮጵያ እና ከእውነታዋ ጎን እንዲቆሙ ለማድረግ ዘመቻውን መቀላቀላቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 

በዘመቻው ከተሳተፉት መካከል ዘላለም መካሻ በዘመቻው በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን የተወጣ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሕይወት ፋንታሁን በበኩላ "የነጩ ፖስታ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዘመቻ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት እንዳላት ተናግራለች።

ሌላው ተሳታፊ ሙሉዬ ዋቅጋሪ "ደብዳቤ በመጻፍ የምናሰማው መልዕክት  ሁሉንም የሚጠቅም  በትግራይ ክልል ውስጥም ያሉ ወጣቶች ያለ ዕድሜያቸው  እየሞቱ ነው፡፡ እነሱንም አገርም ከማዳን አንጻር መታየት ያለበት ዘመቻ ነው" ሲል ተናግሯል።

ወጣቶቹ የአገራቸውን እውነታ ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

ዘመቻው 'አገር የማዳን አንደኛው መንገድ ነው' ያሉት ወጣቶቹ ሌሎች ወጣቶችም ተሳትፎ በማድረግ ከአገራቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ የአገርን እውነታ ለማሳወቅ በሚደረግ ጥረት ወጣቶች በአንድ መንፈስና ስነ-ልቦና መሳተፍ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡

የክፍለ ከተማው የብልጽግና ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደረስ ፈጠነ በበኩላቸው በክፍለ ከተማ ደረጃ በሚካሄደው ዘመቻ ከ200 ሺህ በላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ ታቅዷል ብለዋል።

መርሃ ግብሩ እስከ መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።


በዚሁ ንቅናቄ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እንዲደርስ ይሰራል መባሉን ኢዜአ ትናንት በዘመቻው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ መነገሩን ዘግቧል።

በዘመቻው በአጠቃላይ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም